በኢትዮጵያ የትራንስፖርት ዘርፍ ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን የሚያሰማራ አዲስ አገልግሎት ይፋ ተደረገ

በኢትዮጵያ የትራንስፖርት ዘርፍ ላይ በቴክኖሎጂ የታገዘና ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ብቻ የሚጠቀም አዲስ የትራንስፖርት አገልግሎት በዛሬው ዕለት ስራ ጀምረዋል።

“ዘማይ ጉዞ” እና “ዘማይ ብር” የተሰኙት እነዚህ አዳዲስ አገልግሎቶች በዋናነት የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስና ዘመናዊ የክፍያ ስርአትን ለማስተዋወቅ ያለሙ መሆኑ ተገልጿል።

በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተካሄደው የማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰይድ መሃመድ፣ አገልግሎቱ ስራውን የጀመረው በ1 ሺህ 680 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ነው ብለዋል።

አቶ ሰይድ ተቋሙ በቀጣይ የተሽከርካሪዎቹን ቁጥር ወደ 30,000 ለማድረስ ማቀዱንም ገልፀዋል ።

ይህ አዲስ የትራንስፖርት አማራጭ ከሌሎች የሚለይባቸውን ነጥቦች ያስረዳው መግለጫው፤ ተሽከርካሪዎቹ ድምፅ አልባና ከጭስ ነፃ መሆናቸውን ጠቅሷል።

ከዚህም በተጨማሪ በተሽከርካሪዎቹ ውስጥ የገመድ አልባ ስልክ መሙያ (Wireless Charger) እና የእንፋሎት ማጠቢያ (Steam Washing) ቴክኖሎጂዎች መገጠማቸው ለተሳፋሪዎች የተለየ ምቾት እንደሚፈጥር ተጠቁሟል።

የዋጋ ተመንን በተመለከተም የመነሻ ዋጋው 100 ብር ሆኖ፣ በየኪሎ ሜትሩ የሚታሰበው ክፍያ 12 ብር ብቻ መሆኑ ተገልጿል።

ይህም አገልግሎቱን ተመጣጣኝ ያደርገዋል ተብሏል።

ከጉዞ አገልግሎቱ ጎን ለጎን “ዘማይ ብር” የተሰኘው የዲጂታል ክፍያ መተግበሪያ ስራ የጀመረ ሲሆን፣ ተጠቃሚዎች በመተግበሪያው ሲጠቀሙ የ20 በመቶ ቅናሽ እንደሚያገኙ ተጠቅሷል።

ይህ የክፍያ ስርአት ከሀገሪቱ ባንኮችና ከቴሌ ብር ጋር የተሳሰረ በመሆኑ የገንዘብ ዝውውሩን ቀላል እንደሚያደርገው ታምኖበታል።

ተቋሙ ከትራንስፖርት አገልግሎቱ ባለፈ በሴኮንድ 1 ሚሊዮን ጥሪዎችን ማስተናገድ የሚችል “6312” የተሰኘ ዘመናዊ የጥሪ ማዕከል መክፈቱንና ይህም ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር አስታውቋል።

ልዑል ወልዴ

መጋቢት 20/2018

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *