በዩክሬን ጥቃት ሳቢያ በሩሲያ የነዳጅ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ቃጠሎ መነሳቱን የሳተላይት ምስሎች አሳዩ

የሳተላይት ምስሎች እና የተረጋገጡ ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት፤ ዩክሬን ባለፈው ሳምንት በባልቲክ ባሕር አቅራቢያ በሚገኙ ቁልፍ የሩሲያ የነዳጅ ኤክስፖርት መሠረተ ልማቶች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሰንዝራለች፡፡
ይህም አንዳንድ ተቋማት ለተከታታይ ቀናት እንዲቃጠሉ አድርጓል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ እንዳረጋገጠው፤ ከመጋቢት 23 ጀምሮ ከዩክሬን ድንበር በስተሰሜን 800 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ሴንት ፒተርስበርግ አቅራቢያ በሚገኘው የሩሲያ ሌኒንግራድ ግዛት ቢያንስ ሦስት የነዳጅ ጣቢያዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡

ይህም ቁልፍ የባልቲክ ባሕር ወደቦች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶችን እንዲሁም በአቅራቢያው በሚገኘው የኪሪሺ የነዳጅ ማጣሪያ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ያጠቃልላል።

የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በመጋቢት 26 እና 27 በየትኛዉም የሩሲያ ሦስት የባልቲክ ወደቦች ላይ ነዳጅ የጫነ መርከብ አልነበረም፡፡

ይህም ሞስኮ በ2022 በዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ ከጀመረች ወዲህ ለሁለት ተከታታይ ቀናት እንዲህ ያለ እንቅስቃሴ ሳይኖር ሲቀር የመጀመሪያው መሆኑን ማዕከሉ ገልጿል።

የሳተላይት ምስሎች በመጋቢት 24 በፕሪሞርስክ ከሚቃጠሉ የነዳጅ ተቋማት የሚነሳ ግዙፍ ጭስ፤እንዲሁም በመጋቢት 27 በኡስት-ሉጋ ላይ የደረሰ ቃጠሎ እና በኪሪሺ ላይ የደረሰ ከፍተኛ ጉዳት ያሳያሉ።

የዩክሬን ወታደራዊ ድሮን ኃይሎች አዛዥ ሮበርት ብሮቭዲ፤ ጥቃቶቹ ዓላማቸው የሩሲያን የነዳጅ ደም ወሳጅ ቧንቧዎች የማጣራት አቅም እና የጥሬ ነዳጅ ኤክስፖርት መሠረተ ልማትን ትጥቅ ማስፈታት መሆኑን ተናግረዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ እንደተናገሩት፤ አጋሮቻቸው በዓለም አቀፍ የኢነርጂ ቀውስ ምክንያት ኪቭ በሩሲያ የኢነርጂ ዘርፍ ላይ የምታደርገውን ጥቃት እንድትቀንስ ጠይቀዋል፡፡

ነገር ግን ጥቃቱ የሚቆመው ሩሲያ የዩክሬንን የኢነርጂ ሥርዓት ማጥቃት ስታቆም ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

ሀና ሰይፉ

መጋቢት 22/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *