በአዲስ አበባ ከሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ዉጪ ቀሩ የተባሉ የትግራይ ክልል አጀንዳዎች ካሉ አጀንዳዎች ለማካተት በሩ ክፍት መሆኑን ኮሚሽነር መስፍን አርአያ ገለፁ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በዛሬዉ ዕለት በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል የትግራይ ክልልን የአጀንዳ ማሰባሰብ እንዲሁም የተሳታፊዎች ልየታን እያካሄደ ይገኛል።
ዛሬ ተጀምሮ እስከ ጥር 25 በሚቆየዉ በዚህ ሂደት በዛሬዉ የመክፈቻ ዕለት የትግራይ ክልል ተወላጆች እና በክልሉ የሚገኙ ማህበራት ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች በዚህ መድረክ ላይ ተገኝተዋል።
የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ፤ “በትግራይ ክልልም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች በፖለቲካም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች ያለዉ ሰላም ማጣት ቅቡልነት ያለዉ ሀገረ መንግስት በመገንባት ዙሪያ አለመተማመኖች እንዳሉ ይታመናል” ብለዋል።
በኮሚሽኑ የአሰራር ስርዓት መሠረት የአጀንዳ ማሰባሰብም ይሁን የተሳታፊዎች ልየታን በክልሉ ማድረግ ቢገባም ሂደቱን በክልሉ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ አለመፈጠሩን ከክልሉ ለመጡ ተሳታፊዎች አብራርተዋል።
ዛሬ በአዲስ አበባ በተጀመረው በዚህ ሂደት ከሚነሱ የትግራይ ክልል አጀንዳዎች ዉጪ ቀሪ የተባሉ አጀንዳዎችን ካሉ ኮሚሽኑ እነሱንም ለማካተት የኮሚሽኑ በር ክፍት ነዉ ሲሉ ኮሚሽነር መስፍን አርአያ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ክልላዊም ሆነ ሀገራዊ ጉዳዮች እና ችግሮች በአጀንዳነት መልክ የሚቀርብ መሆኑን ያስረዱ ሲሆን፤ተሳታፊዎች ይህ ሂደት በገለልተኝነት የሚታይ መሆኑንም ለተሳታፊዎች አረጋግጠዋል።
ዛሬ በተጀመረዉ በዚህ የመጀመሪያ ዙር ሂደት ከተሳታፊዎች ዉጪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮምሽን፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴን ጨምሮ ሌሎች በእንግድነት ተሳትፈዋል።
ቁምነገር አየለ
መጋቢት 23/2018 ዓ.ም
