በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየዉ የመጀመሪያዉ ዙር የትግራይ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት በዛሬዉ ዕለት ተጠናቋል።
ኮሚሽኑ በክልሉ ተገኝቶ ሌሎች ሂደቶችን ለማድረግ ለጊዜያዊ አስተዳደሩም ጥሪዉን አቅርቧል።
የክልሉ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት በአዲስ አበባ መካሄድ ብዙ ጥያቄዎች እያስተናገደ ቆይቷል።
በዛሬዉ ዕለት የመርሃግብሩን መጠናቀቅ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ በተሰጠበት ወቅት ኮሚሽነር መላኩ ወ/ ማርያም ጉዳዩ ላይ ምላሽ ሰጥተዋል።
በምላሻቸዉ‹‹አቶ ጌታቸዉ ረዳ ከተሾሙበት ጊዜ አንስቶ ያለመታከት ተነጋግረናል፤ በሌሎች ክልሎች አስተዳዳሪዎች ናቸዉ ገብተን እንድንሰራ ምቹ መደላድል የሚፈጥሩት ፤ አንዳንዶቹ ሳንጠይቅም ገብተን እንድንሰራ ይፈቅዳሉ፤ በትግራይ ያ አልተደረገም››ብለዋል።
አያይዘዉም‹‹ለፃፍነዉ ደብዳቤ እንኳን ግልፅ የሆነ የደብዳቤ ምላሽ አላገኘንም፤ ይሄ ሊሰመርበት ይገባል›› ሲሉ ኮሚሽነር መላኩ ወልደ ማርያም ተናግረዋል።
‹‹አቶ ጌታቸዉ ረዳ የምክክር ሂደቱ በክልሉ ያለመከናወኑን ጥያቄ ሲያነሱ በጣም ነዉ ግርም ያለኝ፤ ያንን ለማድረግ የሚያስችል ስልጣን ባላቸዉ ጊዜ ያን አላደረጉም››ሲሉም አክለዋል ኮሚሽነሩ።
ኮሚሽነር መላኩ ሲቀጥሉም ከዛም በኋላ የተረከቡት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ሀላፊነት ሲወስዱ ሊያከናዉኑ ግዴታ ከገቧቸዉ አንዱ የምክክር ሂደቱን ማሳለጥ እንደነበር ተናግረዋል።
ሆኖም‹‹በተደረገዉ በዛ ሁሉ ዉይይት እሺም የለም እምቢም የሚል መልስ የለም›› በሚል ተደርገዉ የነበሩ ዉይይቶችን አስታዉሰዋል።
ኮሚሽነር መላኩ ወልደ ማርያም‹‹መጨረሻ ላይ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በአምስት ዞኖች መጥታቹ የምክክር ሂደት ማከናወን ትችላላችሁ ብሎ ነግሮን ሲያበቃ፤ ንግግሩ እዉነት መስሎን፤ ባለሙያዎቻችን ስራ እየሰሩ እቅድ ሲያወጡ፣ ፕሮግራም ሲነድፉ እና ሲያዘጋጁ 10 ቀናትን ከቆዩ በኋላ የህጻፅ ጉዳይ መጣ ተባለ በዛ እንዲቆም ተደረገ››በማለት አብራርተዋል።
ኮሚሽነር መላኩ እንደገለፁት፤‹‹እዉነት ለመናገር ሂደቱን የሚያኮላሽ አይደለም፤ በሆነዉ ነገር እናዝናለን የህጻፅ ጉዳይ ግን የስራ ሂደቱን የሚያስቆም አልነበረም››ብለዋል።
የኮሚሽኑን ይህን ሂደት በክልሉ ማድረግ ሳይፈለግ ቀርቶ አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል ያሉት ኮሚሽነር መላኩ፤ ‹‹ፍላጎቱ የለም እዛ››በማለት ገልፀዋል።
‹‹ህወሃት ህጋዊ ሰዉነት እንደሌለዉ ተደርጎ ቢወሰድም፤ እኛ ግን ህጋዊ ሰዉነት እንዳለዉ አካል የህወሃትን አመራሮች አነጋግረናል ፤ ይሄ ኮሚሽኑ ምን ያህል ርቀት እንደሄደ የሚያሳይ ነዉ››ብለዋል።
‹‹በክልሉ ያለዉ አካል ካልፈቀደ ምን አድርገን ነዉ እኛ የምንገባዉ? ግብግብ ልንፈጥር ነዉ? ባለሙያዎቻችንን ችግር ዉስጥ ልንጥል ነዉ? ›› ሲሉ የተደረጉትን ጥረቶች ገልፀዋል።
ኮሚሽር መላኩ ወ/ ማርያም በአዲስ አበባ በተደረገዉ የምክክሩ ሂደት ‹‹በዛ ሊነሱ የሚችሉ ነገሮች በሙሉ እዚህ ተነስተዋል ››በማለት ተናግረዋል።
በአጀንዳ ርክክብ ወቅት እንደተገለፀዉ ፤የክልሉ ተሳታፊዎች 11 ዋና ዋና አጀንዳዎችን እና 51 ዝርዝር አጀንዳዎችን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ርክክብ አድርገዋል።
በዛሬዉ ዕለት በነበረዉ መርሃግብር እንደተገለፀዉ፤ ከክልሉ ከ300 በላይ ተሳታፊዎች እንደነበሩ በመጥቀስ አጠቃላይ ከ700 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙበት ሂደት እንደነበር በኮሚሽኑ ተነግሯል።
ቁምነገር አየለ
መጋቢት 25/2018 ዓ.ም
