ወሳኝ የቀጣናው የውሃ መስመር የሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ ከተዘጋ በኋላ፤ አሁን ደግሞ የባብ ኤል-መንዴብ ወሽመጥ የመስተጓጎል አደጋ ተጋርጦበታል።
የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ በኢራን ተመትታ የወደቀችው አውሮፕላን አብራሪ በአሜሪካ ኃይሎች ከተረፈ በኋላ፤ ኢራን እስከ ማክሰኞ ቀነ-ገደብ ድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥን ካልከፈተች በሀገሪቱ እና በመሰረተ ልማቷ ላይ ጥቃት እንደሚያደርሱ ጠንካራ ቃላት የታከሉባቸውን ዛቻዎች እሁድ ዕለት ሰንዝረዋል።
ኢራን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በጎረቤት የባህረ ሰላጤው አረብ ሀገራት የኢነርጂ መሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃት የፈጸመች ሲሆን፤ በአረብ ባሕረ ገብ መሬት አቅራቢያ የሚገኘውን የባብ ኤል-መንዴብ ወሽመጥንም ለመገደብ ዝታለች።
32 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የባብ ኤል-መንዴብ ወሽመጥ ቀይ ባሕርን ከኤደን ባሕረ ሰላጤ እና ከአረብ ባሕር ጋር ያገናኛል። የዓለም የንግድ ልውውጥ 12 በመቶ ያህሉ አብዛኛውን ጊዜ በዚህ ወሽመጥ በኩል ያልፋል።
በተጨማሪም ለዓለም አቀፍ የነዳጅ ንግድ በጣም ስራ ከሚበዛባቸው መንገዶች አንዱ ነው። እንደ አሜሪካ የኢነርጂ መረጃ ኤጀንሲ ገለጻ፤ ወሽመጡ በ2024 በቀን 4 ሚሊየን በርሜል የሚሆን ድፍድፍ ዘይት ያስተላልፍ ነበር።
የሆርሙዝ ወሽመጥ ከተዘጋ ጀምሮ፤ሳውዲ አረቢያ በቀን በሚሊየን የሚቆጠሩ በርሜል ድፍድፍ ዘይትን በባብ ኤል-ማንዴብ በኩል እየላከች ትገኛለች።
አንድ ከፍተኛ የኢራን ባለስልጣን በኤክስ ማህበራዊ ገፅ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ ዋይት ሀውስ የሞኝነት ስህተቱን ለመድገም ከደፈረ፤የዓለም የኢነርጂ እና የንግድ ፍሰት በአንድ እርምጃ ሊስተጓጎል እንደሚችል በቅርቡ ይገነዘባል” ብለዋል።
ሁቲዎች በቀይ ባሕር ላይ በሚጓዙ መርከቦች ላይ ጥቃት መሰንዘር ሊጀምሩ ይችላሉ የሚል ስጋት እየጨመረ መጥቷል። ኢራን ከየመኑ አማፂ ቡድን ጋር የቅርብ ግንኙነት አላት።
በባብ ኤል-መንዴብ በኩል የሚደረገውን ጉዞ ማስተጓጎል የመርከብ ኩባንያዎች ልክ በ2024 እና 2025 እንዳደረጉት መርከቦቻቸውን በደቡብ አፍሪካ እንዲያዞሩ ያስገድዳቸዋል፤ ይህም ወጪን በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል።
ሀና ሰይፉ
መጋቢት 28/2018 ዓ.ም
