በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ አስተዳደር ዙሪያ የሚያተኩር ሰፊ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
ይህ ውይይት “በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕር ሰላጤ ቀጠና ያለው የባሕር ላይ አስተዳደር፦ አካታችነትና ትብብር ለጋራ ጥቅም” በሚል መሪ ቃል የተሰናዳ ሲሆን፣ በቀጣናው የሚስተዋሉ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የደኅንነት ጉዳዮችን በዝርዝር ለመዳሰስ ያለመ ነው።
ላለፉት ረጅም ዓመታት የቀይ ባሕር አስተዳደር በባሕር ዳርቻ አገራት ብቻ የታጠረ ሆኖ ቢቆይም፣ አሁን ላይ ግን ይህ አካሄድ የቀጣናውን ዘላቂ ሰላምና የጋራ እድገት ሊያረጋግጥ እንደማይችል በስፋት እየታመነበት መጥቷል።
በመሆኑም ለሁሉም ወገኖች የሚተርፍ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ይበልጥ የተሻለና አካታች የሆነ ትብብር አስፈላጊ መሆኑ በውይይቱ ላይ ተገልጿል።
በዚህ ረገድ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት በቀጣናው ሰላምና ደኅንነት ላይ ያላቸው ሚና የማይተካና ከፍተኛ ስለመሆኑ ጥልቅ ትንታኔ መቅረቡን የኢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።
በተጨማሪም በዚህ ውይይት ላይ የኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ መሆን ወሳኝ የሆኑ የኢኮኖሚ ዕድሎችን እንድታጣ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን፣ ቀጣናዊ ሚናዋም እንዲቀንስ ምክንያት መሆኑ ተነስቷል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ሉዓላዊ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት ከአገራዊ ግብ በላይ መሆኑና ለቀጣናው የጋራ ጥቅሞች የሚውል ስለመሆኑ በስፋት ተብራርቷል።
ይህ ጥረት ከአፍሪካ ሕብረት የ2063 አጀንዳ ጋር ሙሉ በሙሉ እንደሚጣጣምም ነው የተመላከተው።
ኢትዮጵያ በባሕር ላይ የሚኖራት ሚና መጠናከሩ እንደ የባሕር ላይ ወንበዴነት፣ ሽብርተኝነት፣ ሕገ-ወጥ ስደት እና የሰዎች ዝውውር ያሉ የጋራ የደኅንነት ሥጋቶችን በጋራ ለመከላከል የሚኖራትን አቅም እንደሚያሳድገው ተገልጿል።
ውይይቱ በዋናነት የባሕር ላይ ደኅንነት እና ትብብርን ማጎልበት፣ የኢኮኖሚ ዕድሎችንና ትስስርን ማሳደግ እንዲሁም አካታች የባሕር ላይ አስተዳደር ለጋራ ጥቅሞች በሚሉ መነሻ ጽሁፎች ላይ በማተኮር የቀጣናውን የወደፊት አቅጣጫ የሚጠቁም ይሆናል።
መጋቢት 29/2018 ዓ.ም
