“የመጀመሪያውና ሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች በአትላንቲክና በፓስፊክ ውቅያኖሶች ላይ እንዳተኮሩ ሁሉ፣ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ከተከሰተ መድረኩ ቀይ ባህርና የሕንድ ውቅያኖስ መሆኑ አይቀሬ ነው” ሲሉ አቶ ዛዲግ አብርሃ ተናገሩ
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ ይህን ያሉት የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በቢሾፍቱ ከተማ ባዘጋጀው ”የሱሉልታ ውሃና የውሃ ዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ“ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡
የጂኦ-ፖለቲካውን ስጋትና ዕድልን በተመለከተ መልከዓ ምድራዉ ሁኔታዎች ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ለታላላቅ ኃያላን ፉክክር ያለውን መሠረታዊ ፋይዳ አስመልክተው በሰጡት ትንታኔ፣ ጂኦግራፊ በአሁኑ ወቅት የዓለም ፖለቲካ ማጠንጠኛ እየሆነ መምጣቱንና ለኢትዮጵያም የባህር በር ጉዳይ የህልውና ያህል ወሳኝ መሆኑን አስምረውበታል።
በአሁኑ ወቅት ዓለም የታላላቅ ኃያላን የፉክክር መድረክ መሆኗን የገለጹት አቶ ዛዲግ፣ በተለይም የባህር መተላለፊያዎች ያላቸውን ስትራቴጂካዊ ዋጋ አብራርተዋል።
እንደ ባበኤል መንደብ፣ ሆርሙዝ እና ማላካ ያሉ ስትራቴጂካዊ ስፍራዎች የዓለምን ፖለቲካ እንደሚወስኑ ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ለባብኤል መንደብ እጅግ ቅርብ መሆኗ ጉዳዩን ቀጥተኛ የቤት ሥራ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይዛ የባህር በር የሌላት ብቸኛ ሀገር መሆኗ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጣረስ (Paradox) መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ የባህር በር ጥያቄው አሁን በድንገት የመጣ ሳይሆን ለዘመናት የቆየ የሕዝብ ሕመም መሆኑን አስታውሰዋል።
ላለፉት ሠላሳ ዓመታት በሀገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የባህር በር ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ የቆየ ቢሆንም፣ አሁን ያለው አመራር ግን ጉዳዩን ቁጥር አንድ ብሔራዊ አጀንዳ በማድረግ ለውጥ እያመጣ ነው ብለዋል።
ይህም ለትውልዱ ስለ ባህር በር አስፈላጊነት ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ፣ ኢትዮጵያ ያለ ባህር በር ዘላቂ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደማትችል በጽኑ እንድታምን አድርጓታል ሲሉም አክለዋል።
አዲስአለም አበበ
መጋት 30/2018 ዓ.ም
