ኢትዮ ቴሌኮም ከኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ – አዳማ የፈጣን መንገድ ላይ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በቴሌብር ዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ለማከናወን የሚያስችል ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራረሙ።
ይህ ስምምነት “ስማርት ሞቢሊቲ”ን (Smart Mobility) በሀገሪቱ የፈጣን መንገዶች ላይ ተግባራዊ ለማድረግና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞን ለማፋጠን ያለመ ነው።
በዚህ አዲስ አሠራር በቴሌብር ሱፐር አፕ ውስጥ የሚገኘው “ቶሎ” (TOLO) የተሰኘ ሚኒ አፕ ከRFID ቴክኖሎጂ ጋር ተቀናጅቶ ሥራ ላይ ውሏል።
ይህም አሽከርካሪዎች ተሽከርካሪዎቻቸው ላይ በሚለጠፍ መለያ አማካኝነት በክፍያ በሮች ላይ ሳይቆሙ በቀጥታ እንዲያልፉ (Non-stop passage) የሚያስችል ሲሆን፣ ክፍያውም ከቴሌብር አካውንታቸው ላይ በራስ-አገዝ ዘዴ ተቀናሽ ይደረጋል።
ደንበኞች እስከ 10 የሚደርሱ ተሽከርካሪዎችን ከአንድ የቴሌብር አካውንት ጋር በማገናኘት ለራሳቸውም ሆነ ለሌሎች የክፍያ ሂሳብ መሙላት ይችላሉ።
ከመንገድ አጠቃቀም ክፍያ በተጨማሪም እንደ ንብረት ውድመት ካሳ፣ የክሬን እና የተሽከርካሪ ማቆሚያ ክፍያዎች እንዲሁም የጭነት ክብደት መጣስን ጨምሮ ልዩ ልዩ የቅጣት ክፍያዎች በዚህ ዲጂታል ሥርዓት ውስጥ ተካተዋል።
ይህ አሠራር ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩትን የጥሬ ገንዘብ አያያዝ ሥጋቶች፣ በእጅ የሚከናወኑ አድካሚ የምዝገባ ሂደቶችን እና በክፍያ በሮች ላይ የሚፈጠሩ የትራፊክ መጨናነቆችን ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር ነው።
ኢንተርፕራይዙ የገቢ አሰባሰቡን በቅጽበት (Real-time) ለመከታተልና የአሠራር ግልጽነትን ለማስፈን የሚያስችለው ይህ ቴክኖሎጂ፣ የ“ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” ስትራቴጂን ለማሳካት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ተገልጿል።
ኢትዮ ቴሌኮም “ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር” በሚለው መሪ ቃሉ መሠረት የዜጎችን ሕይወት የሚያቀልሉ መሰል የዲጂታል መፍትሄዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል።
ዘገባው የካሪቡ አውቶሞቲቨ ነው።
