ታዋቂው አትሌትና ባለሀብት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ በደብረ ብርሃን ከተማ ያስገነባው 11ኛው የኃይሌ ሆቴልና ሪዞርት ፕሮጀክት በዛሬው ዕለት ተመረቀ።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የደብረ ብርሃን ከተማ ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት፣ የሆቴሉ መከፈት ለከተማዋ የቱሪዝም ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍትና የከተማዋን የዕድገት ትንሣኤ የሚያበሥር መሆኑን ገልጸዋል።
ከንቲባው በንግግራቸው ሻለቃ ኃይሌ በሩጫው ዓለም የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባዮች ከፍ አድርጎ እንዳውለበለበው ሁሉ፣ ዛሬ ደግሞ በኢንቨስትመንትና በልማት ግንባር ቀደም በመሆን በደብረ ብርሃን ምድር ላይ ታሪካዊ አሻራውን በማሳረፉ ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበውለታል።
ሻለቃ ኃይሌ “ተስፋ አስቆራጭ ቃላትን በተግባርና በላብ ያጠፋ ለትውልድ አርዓያ የሚሆን ጀግና” መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።
ደብረ ብርሃን በአፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት በ1446 ዓ.ም የተመሠረተች ጥንታዊ የጥበብና የመንፈሳዊ ማዕከል መሆኗን ያስታወሱት አቶ በድሉ፣ ዛሬ ደግሞ ከተማዋ ከ600 ዓመታት በኋላ የኢንዱስትሪ፣ የቱሪዝም እና የእውቀት ማዕከል ለመሆን በትኩረት እየተሠራባት መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህ ረገድ የኃይሌ ሆቴል መመረቅ ለከተማዋ የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴና ለቱሪዝም ዕድገት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል።
እንደ ከንቲባው ገለጻ፣ ይህ ዘመናዊ ሆቴል የከተማዋን ውበት ከመጨመር ባለፈ የሆቴልና የቱሪዝም አገልግሎት ደረጃን ወደ ላቀ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሸጋግራል ተብሎ ይጠበቃል።
በተጨማሪም ለኢንዱስትሪ ባለቤቶችና ለባለሀብቶች ምቹ የሥራ አካባቢ በመፍጠር፣ ለውጭና ለአገር ውስጥ ቱሪስቶች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠትና ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ የጎላ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
ሌሎች ባለሀብቶችም የሻለቃ ኃይሌን ፈር ቀዳጅነት ተከትለው በደብረ ብርሃን ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የከተማ አስተዳደሩም ወደፊት ለሚከናወኑ መሰል የልማት እንቅስቃሴዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
በሆቴል ምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ መካሻ አለማየሁ፣ ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴና ባለቤቱ ወይዘሮ አለም ጥላሁን፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የከተማዋ ነዋሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
አዲስአለም አበበ
ሚያዚያ 15/2018 ዓ.ም
