103 አዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆኑ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ዘጠኝ ወራት 103 አዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ አድርጓል፡፡

አገልግሎቱ ፍትሃዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ባከናወነው ዘርፈ-ብዙ ስራ ከዋናው ግሪድና ከግሪድ የራቁ በርካታ አዳዲስ አካባቢዎችን ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን፤ ከጤናና ማህበራዊ ተቋማት በተጨማሪ ከ31 ሺህ በላይ አባዎራዎችና እማዎራዎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲጠቀሙ አስችሏል፡፡

በዚህም በዘጠኙ ወራት ተጠቃሚ ከሆኑት ውስጥ 82ቱ ከዋናው የኤሌክትሪክ መረብ (ግሪድ) እንዲሁም 21 የገጠር ከተሞችና መንደሮችን ደግሞ በፀሃይ ኃይል አማራጭ (ኦፍግሪድ) የተገናኙ ናቸው፡፡

በተጨማሪም ተደራሽነትን ከማረጋገጥ አኳያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 423 ሺህ 200 አዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ አፈፃፀሙ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ18 ነጥብ 6 በመቶ ብልጫ ያለው ነው፡፡

ኃይል ከተገናኘላቸው አዳዲስ ደንበኞች ውስጥ 31 ሺህ 298 ያህሉ አዲስ የኤሌክትሪክ ተደራሽ በሆኑት የገጠር ከተሞችና መንደሮች ተጠቃሚ የሆኑ ናቸው፡፡

አዲስ ኤሌክትሪክ ካገኙ ደንበኞች መካከል 74 ነጥብ 2 ከመቶ የድህረ ክፍያ እንዲሁም 25 ነጥብ 8 በመቶ የቅድመ ክፍያ ቆጣሪ ተጠቃሚ ናቸው፡፡

ያለፉት ዘጠኝ ወራት አፈፃፀም ጨምሮ በአሁን ወቅት አጠቃላይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ ደንበኞች (እማዎራዎች/አባዎራዎች) ቁጥር 5.64 ሚሊዮን ደርሷል፡፡

ሚያዚያ 26/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *