እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከተደረገ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ቤሩትን ደበደበች

እስራኤል ባለፈው ወር ከሂዝቦላህ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ከደረሰች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በቤሩት ላይ ጥቃት ፈጽማለች።

እስራኤል በጥቃቱ ያነጣጠረችው በከተማዋ ደቡባዊ ዳርቻ በሚገኘው የሚሊሻ ቡድኑ የልዩ “ራድዋን” ኃይል አዛዥ ላይ መሆኑን ገልጻለች።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ጥቃቱን በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን አዛዡ በጥቃቱ መገደሉን የዘገቡ ቢሆንም፤ ከእስራኤል ጦርም ሆነ ከሂዝቦላህ የተሰጠ ማረጋገጫ ግን የለም።

ይህ በሊባኖስ የተደረገው የተኩስ አቁም በዩናይትድ ስቴትስ እና በኢራን መካከል ላለው ሰፊ የተኩስ ማቆም ስምምነት እንደ መሠረት ተቆጥሮ የቆየ ሲሆን፤ በእስራኤል የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዲቆሙ ማድረግ የኢራን ዋነኛ ጥያቄ ነበር።

ኢራን እና አሜሪካ በመካከላቸው ያለውን ግጭት ለማቆም ወደ ስምምነት እየተቃረቡ መሆኑን በሚናገሩበት በዚህ ወቅት፤ይህ ጥቃት በቤሩት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን አቁሞ የነበረውን ስምምነት አደጋ ላይ ጥሎታል።

የእስራኤል ወታደሮች ከሊታኒ ወንዝ በስተደቡብ በሚገኙ አካባቢዎች የቆዩ ሲሆን፤ በደቡብ ሊባኖስም ጥቃቶች ቀጥለዋል።

የኢራን ወዳጅ የሆነው ሂዝቦላህ ወደ እስራኤል ወታደሮች ድሮኖችን በመተኮስ ምላሽ ሰጥቷል።

የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋፍ ሰላም እንደተናገሩት፤ በሊባኖስና በእስራኤል መካከል ስለሚደረግ ማንኛውም ከፍተኛ ደረጃ ስብሰባ መናገር ጊዜው አይደለም የተኩስ አቁሙን ማጠናከር በዋሽንግተን ለሚደረገው አዲስ ድርድር መሠረት እንደሚሆንም ገልጸዋል።

ባለፈው ወር ዋሽንግተን በእስራኤል እና በሊባኖስ አምባሳደሮች መካከል ሁለት ስብሰባዎችን አስተናግዳለች።
ሂዝቦላህ ግን እነዚህን ግንኙነቶች አጥብቆ ተቃዉሟል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተኩስ አቁሙ ለሦስት ሳምንታት መራዘሙን ሲያበስሩ፤ ኔታንያሁ እና የሊባኖሱ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አውንን በቅርቡ ለማስተናገድ እንደሚጠብቁና በዘንድሮው ዓመት የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ “ትልቅ ዕድል” እንዳለ ገልጸው ነበር።

እንደ ሮይተርስ አገባ ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊባኖስ የምትፈልገው “ከእስራኤል ጋር ግንኙነትን ‹‹መደበኛ›› ማድረግ ሳይሆን ሰላም ማምጣት ነው፡፡

ሀና ሰይፉ

ሚያዚያ 29/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *