ኢትዮጵያ ለገበያ ከምታቀርበው ምርት ውስጥ 45 በመቶ የሚሆነው ደረጃውን የጠበቀ ማከማቻ በማጣቱ ለከፍተኛ ብክነት የተጋለጠ መሆኑ ተነገረ

ኢትዮጵያ 27 ሚሊየን ኩንታል ብቻ ሊያከማች የሚችል ደረጃዉን የጠበቀ የምርት ማከማቻ መጋዘን ያላት መሆኑ ተነግሯል።

በሀገሪቱ የገጠር አካባቢዎች የሚስተዋለው የምርት መጋዘን እጥረት ማሳያነት ለ45 በመቶ ያህሉ  ምርት ማከማቻ  የሚሆን መጋዘን የሌላት  መሆኑ ተገልፆል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የምርት ማከማቻ መጋዘኞች አለመኖር እንዲሁም ደረጃቸዉ ዝቅ ማለት ለምርት ብክነት ምክንያት እየሆነ መምጣቱን  ገልፆል።

ኢንስቲትዩቱ ይህን ያለዉ  ሚያዝያ 29 ቀን 2018 አ.ም በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አዘጋጅነት ” የገጠር ትራንስፎርሜሽን በኢትዩጵያ፤ ከግብርና ወደ መዋቅራዊ ለዉጥ ሽግግር መግቢያ” በሚል በተደረገ የዉይይት መድረክ ላይ ነዉ።

በዉይይት መድረኩ ገለፃ ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ማንደፍሮ  ንጉሴ ከሁለት አመት በፊት ማለትም በ2016 አ.ም የነበረዉ መረጃ በማጣቀሻነት ለመድረኩ አስረድተዋል።

በዚህም 1 መቶ 16 ሚሊየን ኩንታል ለገበያ የሚቀርብ ምርት አለ የሚል መረጃ እንዳለ ጠቁመዋል።

ዶ/ር ማንደፍሮ እንደገለፁት ” ከዚህ ዉስጥ 13 ሚሊየን ኩንታሉ ቀጥታ ከማሳ ወደ ገዥ የሚሄዱ ናቸዉ ለምሳሌ እንደ ቢራ ገብስ እና አኩሪ አተር እንዲሁም አቮካዶ  ያሉ ምርቶች መጋዘን የማይፈልጉ በቀጥታ ከእርሻ ወደ ፋብሪካ ነዉ የሚሄዱት” ሲሉ  ይገልፃሉ።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ ቀሪ 103 ሚሊየኑ የምርት ማከማቻ መጋዘን የሚፈልጉ ናቸዉ። እንደ ሀገር  ለዚህ ምን አለ? ሲሉ ጠይቀዋል።

ዶ/ር ማንደፍሮ በማብራሪያቸው” ከዚህ ዉስጥ 55 በመቶዉ ብቻ ምርት ማከማቸት የሚችል መጋዘኞች ነዉ ያለን ቀሪዉ 45 በመቶ ልናከማችበት የምንችል መጋዘን በመጋዘን ስም የለንም” ሲሉም አክለዋል።

በየቤቱ በረንዳ ላይ የሚቀመጡ ምርቶች የተለፋባቸዉን ያህል ጥሩ ገቢ ማስገባት ሲገባቸዉ ለምርት ብክለት የሚጋለጡ ይሆናል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ማንደፍሮ ንጉሴ እንዳሉት ” አሉ ከተባሉት 55 በመቶ የምርት መጋዘኞችን ወስደን ስናይ ደረጃዉን የጠበቀ እና ያልጠበቀ ዝም ብሎ መጋዘን ነዉ ስንል 27 ሚሊየን ኩንታል ብቻ ሊያከማች የሚችል ደረጃዉን የጠበቀ የምርት ማከማቻ መጋዘን ብቻ ነዉ ያለዉ” ሲሉ አክለዋል።

ከተማ ዉስጥ ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለሀብቶች ወደ ገጠር በመግባት የመጋዘን መሠረተ ልማት ላይ ፈሰስ ቢያደርጉ ትርፋማ ሊሆኑበት የሚችል እድል አለ ተብሏል።

ቁምነገር አየለ

ግንቦት 03/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *