የኢትዮጵያን የግብርና ዘርፍ ለማዘመን እና አገራዊ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የተባለለት የመጀመሪያው አገር አቀፍ የሰብል ጥበቃ እና ማዳበሪያ ኤክስፖ ከግንቦት 14 ቀን እስከ ግንቦት 16 ቀን 2018 በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ሊካሄድ ነው።
ዝግጅቱን የሚያስተባብረው ዊ-ሊንክ የተሰኘው ሀገር በቀል ድርጅት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የኤክስፖው ዋና ዓላማ የአርሶ አደሩን አቅም በዘመናዊ እውቀትና ቴክኖሎጂ በመገንባት የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ነው።
ግሮው ኢትዮጵያ በሚል ስያሜ በሀገሪቱ በዓይነቱ ልዩ እና የመጀመሪያ ሆኖ የተዘጋጀው ይህ አገር አቀፍ ኤክስፖ፤ የኢንዱስትሪውን ዋና ዋና ባለድርሻ አካላት፣ የግብርና ግብዓት አስመጪዎችና አከፋፋዮች፣ ፖሊሲ አውጪ የመንግስት ተቋማትን እንዲሁም አምራች አርሶ አደሮችን በአንድ መድረክ ላይ ያገናኛል ተብሏል።
እነዚህ በዘርፉ የተሰማሩ ቁልፍ ተዋናዮች በአንድ መድረክ ላይ መገናኘታቸውም፣ ጠንካራ የገበያ ትስስር ከመፍጠሩም ባሻገር፤ የቴክኖሎጂ፣ የልምድ እና የእውቀት ሽግግር ለማድረግ ሰፊና ምቹ አጋጣሚን እንደሚፈጥር አዘጋጆቹ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ልዑል ወልዴ
ግንቦት 04 /2018 ዓ.ም
