ዋሽንግተን ለታይዋን የምታቀርበዉን የጦር መሣሪያ ሽያጭ ቻይና አወገዘች

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት ቤጂንግ ከመድረሳቸው ቀደም ብሎ፤ ዋሽንግተን ለታይዋን የምታደርገውን የጦር መሳሪያ ሽያጭ እንድታቆም ቻይና አሳሰባለች።

የታይዋን ጉዳይ በፕሬዝዳንት ትራምፕ እና በቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ምክክር ላይ ዋነኛው አጀንዳ መሆኑ አይቀሬ ነዉ ተብሏል።

አሜሪካ ከታይዋን ጋር ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ባይኖራትም፤ባለፈው ታህሳስ ወር የ11 ቢሊየን ዶላር የጦር መሳሪያ ሽያጭ ጥቅል ይፋ ማድረጓ ይታወሳል።

የቻይና-ታይዋን ጉዳዮች ቢሮ ቃል አቀባይ ዣንግ ሃን፤ የታይዋን ጉዳይ የቻይና የውስጥ መስመር መሆኑን ገልጸው አሜሪካ የምታደርገውን ወታደራዊ ትስስር በፅኑ እንደሚቃወሙ አስታውቀዋል።

አሜሪካ በ‹‹አንድ ቻይና›› ፖሊሲዋ ስር በታይዋን ሉዓላዊነት ላይ ይፋዊ አቋም ባትይዝም የቤጂንግን አቋም ግን ሳትቀበል እውቅና ሰጥታለች።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቻይናን የሚጎበኙት፣ የታይዋን ፓርላማ የፕሬዝዳንት ላይ ቺንግ-ቴን የ40 ቢሊየን ዶላር ልዩ የመከላከያ በጀት ጥያቄ ሁለት ሶስተኛውን ብቻ ካፀደቀ ከአንድ ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ነው።

ይህ የተቆረጠ በጀት ለአሜሪካ የጦር መሳሪያ ግዥ የሚውል ቢሆንም የሀገር ውስጥ የድሮን ፕሮግራሞችን የቀነሰ በመሆኑ ዋሽንግተን ማዘኗን ገልጻለች።

የታይዋን ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣን እንደተናገሩት፤ለታይፔ ትልቁ ስጋት ቻይና ይህንን የተቀነሰ በጀት በትራምፕ ላይ እንደ መደራደሪያ ልትጠቀምበት መቻሏ ነው።

ቻይና የታይዋን ምክር ቤት የጦር መሳሪያ መግዛትን እንደሚቃወም በመሞገት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለታይዋን የሚያደርጉትን የመከላከያ ድጋፍ እንዲቀንሱ ልታግባባ ትችላለች ሲሉ ባለስልጣኑ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ሳራ ዮሐንስ

ግንቦት 05/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *