ትራምፕ የሰማይ ቤተ መቅደስን የጎበኙ ሁለተኛው በስልጣን ላይ ያሉ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነዋል
ትራምፕ እና ሺ ጂንፒንግ አስጎብኚው ስለ ስፍራው በዝግታ በሚያስረዳቸው ወቅት፣ አብረው ቀስ እያሉ ወደ ሰማይ ቤተ መቅደስ አመሩ።
ሁለቱ መሪዎች ንጉሠ ነገሥታት ለመልካም ምርት ይጸልዩበት በነበረውና አስደናቂ ሰማያዊና ወርቃማ ቀለማት ባለው የንጉሣዊ ሕንፃ ፊት ለፊት ሲቆሙ፣ የተቀሩት የልዑካን ቡድን አባላት በጥቂት እርምጃዎች ርቀው ወደ ፓርኩ ተጠግተው ቆመው ነበር።
ትራምፕ አስጎብኚውን በትኩረት ሲያዳምጡ ሺ ጂንፒንግ ፈገግ ብለው ይታዩ ነበር፡፡
ቢቢሲ በዘገባው እንዳሰፈረው የጋዜጠኞች ቡድን ለትራምፕ ውይይቱ እንዴት እየሄደ እንደሆነ ለጠየቋቸው ጥያቄ “በጣም ጥሩ” በማለት መለሱ።
ሁለተኛ ጠያቂ ስለ ታይዋን ተወያይተው እንደሆነ ሲጠይቃቸው፣ ትራምፕ የቀደመውን ሃሳባቸውን በመቀጠል “ግሩም ቦታ ነው፣ አስደናቂ ነው፣ ቻይና ውብ ነች” አሉ።
ስለ ታይዋን በድጋሚ ሲጠየቁ፣ ትራምፕ ልክ እንደ ሺ ሁሉ ዝም ብለው ወደ ፊት ትኩር ብለው ተመለከቱ።
ጥያቄው ለሦስተኛ ጊዜ የቀረበው ሁለቱ መሪዎች ዞረው ወደ ቤተ መቅደሱ ደረጃዎች መራመድ ከጀመሩ በኋላ ነበር።
በ15ኛው ክፍለ ዘመን በሚንግ ስርወ መንግስት ዘመን የተገነባው ይህ ቤተ መቅደስ፣ በሰማይና በምድር መካከል ያለውን ግንኙነት ያመለክታል። በሚንግ እና በቺንግ ስርወ መንግስታት የነበሩ ንጉሠ ነገሥታት ለሰማይ መስዋዕት ለማቅረብ እና የተትረፈረፈ ምርት እንዲኖር ለመጸለይ ወደ ቤተ መቅደሱ ይመላለሱ ነበር።
በዘመናዊ ታሪክ ውስጥም ስፍራው ታዋቂ የሆኑ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን አስተናግዷል። ትራምፕ ቤተ መቅደሱን የጎበኙ ሁለተኛው በሥልጣን ላይ ያሉ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ፤ የመጀመሪያው በ1975 (እ.ኤ.አ) የጎበኙት ጄራልድ ፎርድ ነበሩ።
በ1970ዎቹ በቤጂንግ እና በዋሽንግተን መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ መደበኛ ሁኔታ ለመመለስ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት አሜሪካዊው ዲፕሎማት ሄንሪ ኪሲንጀር፣ እንደ ቻይና መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ከሆነ ስፍራውን 15 ጊዜ ጎብኝተውታል ።
ግንቦት 06/2018 ዓ.ም
