የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 23ኛ መደበኛ ስብሰባ፣ ለአርብቶ አደሩ የምግብ ዋስትና እና ለስድስተኛው ምዕራፍ የልማት ሴፍቲኔት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውሉ ሁለት የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል።
ምክር ቤቱ በመጀመሪያ የተመለከተው በኢትዮጵያ መንግሥት እና በአፍሪካ ልማት ባንክ መካከል የተደረገውን የብድር ስምምነት ነው።
ይህ ብድር “ለአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ የመቋቋም አቅም ግንባታ እና የኑሮ ዘይቤ ማሻሻያ” ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል መሆኑ ተገልጿል።
አሁን የጸደቀው የ71 ሚሊየን 9መቶ40 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ብድርም ቀደም ሲል በክፍል አንድ ያልተካተቱ ተጨማሪ የልማት ሥራዎችን በማካተት የአርብቶ አደሩን የአደጋ ተጋላጭነት የመቋቋም አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚውል ነው።
ብድሩ ከወለድ ነፃ ሆኖ፣ የ10 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ40 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ በመሆኑ ከአገሪቱ የብድር ስትራቴጂ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጣጣም መሆኑ ተገልጿል።
ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ ረቂቅ አዋጁን በአዋጅ ቁጥር 1423/2018 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለስድስተኛው ምዕራፍ የልማት ሴፍትኔት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት መርምሮ አጽድቋል።
የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ በሰጡት ማብራሪያ፤መንግስት በምግብ እጥረት ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ከዕርዳታ ጥገኝነት አውጥቶ ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ ስድስተኛው ምዕራፍ ፕሮጀክት በ12 ክልሎችና በአንድ የከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ 4መቶ94 ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
ምክር ቤቱ ይህንኑ የብድር ስምምነት አዋጅ ቁጥር 1424/2018 አድርጎ በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።
ግንቦት 27/2018 ዓ.ም
