የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ቪዛ ኩባንያ በጋራ በመሆን ያዘጋጁትን አዲስ የቪዛ ቅድመ ክፍያ ካርድ በይፋ አስተዋውቀዋል።
ይህ አዲስ የጋራ ብራንድ ካርድ በተለይ ወደ ውጭ ሀገር ለሚጓዙ ኢትዮጵያውያን እና የአየር መንገዱ ደንበኞች የሚያጋጥሟቸውን የክፍያ ችግሮች ለመቅረፍ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።
በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮርፖሬት አገልግሎቶች ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ፤ ባንኩ ከታላላቅ ተቋማት ጋር በመተባበር የዲጂታል ክፍያ ስርዓቱን ለማዘመን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ካርዱ ደንበኞች በውጭ ሀገር በሚቆዩበት ወቅት በፖስ ማሽኖች ክፍያ እንዲፈጽሙ፣ ከኤቲኤም ገንዘብ እንዲያወጡና በዓለም አቀፍ የኢ-ኮሜርስ ድረ-ገጾች ላይ ግብይት እንዲያከናውኑ ያስችላቸዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የንግድ ዘርፍ ዋና መኮንን አቶ ለማ ያደቻ በበኩላቸው፤ ካርዱ በተለይ ለሼባ ማይልስ አባላት ልዩ የምስጋና ስጦታ መሆኑን ገልጸዋል።
ቪዛ ካለው ዓለም አቀፍ ተሞክሮ በመነሳት የኢትዮጵያን የዲጂታል ክፍያ ስነ-ምህዳር ለማጠናከር ከአገር በቀል ተቋማት ጋር መስራቱን እንደሚቀጥል የተናገሩት ደግሞ የቪዛ ኩባንያ የምስራቅ አፍሪካ እና የኢትዮጵያ ስራ አስፈፃሚ አቶ ያሬድ እንዳለ ናቸው።
ይህ አጋርነት የሀገሪቱን የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር ከማፋጠን ባለፈ፣ ለተጓዦች እና ለንግዱ ማህበረሰብ ዘመናዊ እና ምቹ የክፍያ አማራጭ እንደሚፈጥር ተገልጿል።
አዲስአለም አበበ
ግንቦት 28/2018 ዓ.ም
