አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት መክፈት ከጀመሩ 100 ቀናት ያስቆጠሩ ሲሆን፤ በዋሽንግተን ጥያቄ መሰረት እንደ ፕላኔት ላብስ ያሉ ኩባንያዎች በፎቶዎች ላይ እገዳ ጥለው ነበር።
ነገር ግን እገዳው ከመተግበሩ በፊት ከኤርባስ፣ ሴንቲነል እና ቫንተር ሳተላይቶች የተገኙ ምስሎች የደረሰውን ጥፋት በግልጽ አሳይተዋል።
የአልጄዚራ ክፍት መረጃ ምንጭ እነዚህን ምስሎች በማቀናጀት በኢራን፣ ሊባኖስና በባህረ ሰላጤው ላይ የሚገኙ 15 ቁልፍ የጥቃት ቦታዎችን ይፋ አድርጓል።
በዚህም መሰረት በኢራን የሚገኘው የናታንዝ ትልቁ የዩራኒየም ማበልጸጊያ ተቋም ከመሬት በታች ባሉ ክፍሎቹና መግቢያ መንገዶቹ ላይ ከፍተኛ መዋቅራዊ ጉዳት ደርሶበታል።
ለነዳጅ ኤክስፖርት ወሳኝ በሆነችው የሲሪ ደሴት ላይም አንድ ሚሊየን በርሜል ነዳጅ የሚይዘው ግዙፍ ታንከር በጥቃቱ መጋየቱ ተረጋግጧል ነው የተባለው።
በተጨማሪም በሆርሙዝ ባህረ ሰላጤ አቅራቢያ በሚገኘው የባንደር አባስ ወደብ 11 ቦታዎች፣ መጋዘኖችና አንዲት መርከብ ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል።
በፋት የአየር ጦር ሰፈር የድሮንና ሄሊኮፕተር ማዕከላት ላይ የጣሪያዎች መደርመስና የቃጠሎ አደጋዎች ሲታዩ፣ በባህር ኃይል ሰፈር ደግሞ ‹‹አይሪስ ማካራን›› የተባለችው የጦር መርከብ ተመትታ ጥቅጥቅ ያለ ጢስ ሲወጣት ታይቷል።
በሌላ በኩል ጥቃቱ በሊባኖስ ላይም የከፋ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፤ የተመድ የሰላም አስከባሪ ዋና መሥሪያ ቤት በሚገኝበት ናቁራ አካባቢ ከ100 በላይ ህንጻዎች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል።
የደቡብ ሊባኖስ ታሪካዊ መዲና በምትባለው ቢንት ጅቤል ከተማም በእስራኤል የምድርና የአየር ጥቃት ምክንያት ወደ 7መቶ25 የሚጠጉ ህንጻዎችና ተቋማት ላይ ከባድ የፍርስራሽ ጉዳት መድረሱን የሳተላይት ምስሎቹ በግልጽ አሳይተዋል ሲል አልጄዚራ ዘግቧል።
ሳራ ዮሐንስ
ሰኔ 01/2018 ዓ.ም
