በፊሊፒንስ በተከሰተ ርዕደ መሬት የ19 ሰዎች ህይወት አለፈ

በፊሊፒንስ የተከሰተው እና በሬክተር ስኬል 7.8 የተመዘገበውን ኃይለኛ ርዕደ መሬት ተከትሎ ቢያንስ 19 ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል።

የፖሊስ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ አደጋው እስካሁን ቢያንስ በ1መቶ29 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት አድርሷል።

ፊሊፒንስን ኢንዶኔዥያን እና ጃፓንን ጨምሮ በግዛቱ አቅራቢያ የሚገኙ በርካታ ሀገራት የሱናሚ ማስጠንቀቂያ አውጥተው የነበረ ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት ግን አብዛኛዎቹ ማስጠንቀቂያዎች ተነስተዋል።

የፊሊፒንስ የርዕደ መሬት ጥናት ኢንስቲትዩት እንዳስታወቀው ከሆነ ርዕደ መሬቱ የተነሳው 10 ኪሎ ሜትር ያህል ጥልቅ በሆነ ምድር ውስጥ ነው።

የፊሊፒንስ ፕሬዝዳንት ፈርዲናንድ ማርኮስ ጁኒየር ፤ ‹‹ሁሉም የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በአስቸኳይ እርምጃ እንዲወስዱ መመሪያ ሰጥቻለሁ›› ያሉ ሲሆን፤ ህዝቡም ጥንቃቄ በማድረግ ወደ ከፍታ ቦታዎች እንዲሸሽ አሳስበዋል።

ፊሊፒንስ በጂኦሎጂካል አቀማመጧ አለመረጋጋት በሚታይበት የፓሲፊክ የእሳት ቀለበት ላይ የምትገኝ በመሆኗ መሰል የርዕደ መሬት አደጋዎች በተደጋጋሚ ያጋጥሟታል።

ምንም እንኳን አብዛኛዎቹ የመሬት መንቀጥቀጦች ያለምንም ከፍተኛ ጉዳት የሚያልፉ ቢሆንም አንዳንዶቹ ግን ለህልፈተ ህይወት የሚዳርጉ ናቸው ፡፡

በቅርቡም በማዕከላዊ ቪሳያስ ግዛት ውስጥ የተከሰተው የሬክተር ስኬል መጠኑ 6.9 የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ ከ70 በላይ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል፤በተጨማሪም በሚንዳናኦ ዳቫኦ ኦሬንታል የባህር ዳርቻ ላይ የተከሰቱ ሁለት ተከታታይ ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጦች የሌሎች ስምንት ሰዎችን ህይወት መቅጠፋቸዉ ይታወሳል፡፡

ሀና ሰይፉ

ሰኔ 01/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *