የመፍትሔው ረቂቅ አዋጅም በፓርላማ የሕዝብ ውይይት ተደርጎበታል
ኢትዮጵያ በሥርዓተ-ምግብ መጓደል ምክንያት በየዓመቱ 55.5 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ከፍተኛ ሀብት እንደምታጣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተካሄደ ይፋዊ የሕዝብ ግልጽ ውይይት ላይ ተገለጠ።
የምክር ቤቱ የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባሕልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ፣ በሀገሪቱ ያለውን የምግብ ሥርዓት ፖሊሲ በሕግ መደገፍ የሚያስችለው አዲሱ “የምግብ ሥርዓትና ሥርዓተ-ምግብ ረቂቅ አዋጅ” ላይ ሰፊና ጥልቅ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ መግቢያ ላይ እንደተብራራው፣ የምግብ እጥረትና በሕፃናት ላይ የሚከሰተው መቀንጨር በሀገሪቱ ላይ እያደረሰ ያለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። በተለይም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ አጠቃላይ የመቀንጨር ምጣኔ 39 በመቶ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህ አኃዝ በትውልድ ምርታማነትና በሀገር ዕድገት ላይ እያሳደረ ያለው ጫና የላቀ በመሆኑ አፋጣኝ የሕግ ማዕቀፍ ማስፈልጉ ተጠቁሟል።
በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የምክር ቤት አባላትና የዘርፉ ባለሙያዎች በረቂቅ አዋጁ ይዘት ላይ የተለያዩ መሠረታዊ ነጥቦችንና ስጋቶችን አንስተው ሰፊ ውይይት አድርገዋል። መቀንጨር የሚባለው ዘላቂ የአካልና አእምሮ ዕድገት መግታት ችግር የሚከሰተው ከእናቱ ማህፀን ጀምሮ ሕፃኑ እስከ ሁለት ዓመት ዕድሜው ባለው ወሳኝ ጊዜ ውስጥ በመሆኑ፣ ረቂቅ አዋጁ በዚህ የመጀመሪያዎቹ 1,000 ቀናት የዕድሜ ክልል ላይ ልዩ ትኩረትና ጥበቃ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተጨማሪም አዋጁ በትምህርት ቤት ምገባ ላይ ትልቅ ትኩረት መስጠቱ የሚደነቅ ቢሆንም፣ የልጆችን የምግብ ዋስትና በዘላቂነት ለማረጋገጥና የአቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር ያለው ተቋማዊ ቅንጅት ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባ ተገልጿል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከመድረኩ ተሳታፊዎች ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ ከተካሄደው የሕዝብ ውይይት የተገኙት ጠቃሚ ግብዓቶች ረቂቅ አዋጁን ይበልጥ ለማበልጸግና ክፍተቶቹን ለመሙላት ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ይህ አዲስ “የምግብ ሥርዓትና ሥርዓተ-ምግብ አዋጅ” በምክር ቤቱ ታይቶ ሲጸድቅ፣ በሀገሪቱ የተቀረጸውን የምግብ ሥርዓት ፖሊሲ በቀጥታ ወደ ተግባር ለመለወጥ ብሎም ዜጎች በየትኛውም አካባቢ የተመጣጠነ፣ ጤናማና ደኅንነቱ የተጠበቀ ምግብ እንዲያገኙ ለማስቻል ትልቅ መሠረት እንደሚጥል ይጠበቃል።
ለዓለም አሰፋ
ሰኔ 09/2018 ዓ.ም
በሥርዓተ-ምግብ መጓደል ሳቢያ በየዓመቱ 55.5 ቢሊዮን ብር እንደሚባክን ተገለጠ
