የዩክሬን ድሮኖች የሞስኮ የነዳጅ ማጣሪያ ላይ ዛሬ በድጋሚ ጥቃት ሰነዘሩ

የዩክሬን ድሮኖች በሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ በሚገኝ የነዳጅ ማጣሪያ ጣቢያ ላይ በዚህ ሳምንት ለሁለተኛ ጊዜ ከባድ ጥቃት ሰንዝረዋል፡፡

ይህም ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ጦርነቱን ለማቆም ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ከአውሮፓ መሪዎች ጋር የሰላም ስምምነት ድጋፍ ለማግኘት ውይይት ባደረጉ ማግስት ነው።

የሩሲያ ባለስልጣናት በርካታ ድሮኖችን ማክሸፋቸውን ቢገልጹም ማጣሪያው መመታቱን የከተማዋ ከንቲባ ሰርጌይ ሶቢያኒን አረጋግጠዋል።

ይህ ጥቃት ቀደም ሲል በነዳጅ እጥረት ስጋት ውስጥ የነበረችው ሩሲያ ለመጀመሪያ ጊዜ በባህር ላይ ነዳጅ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት እንድትገደድ አድርጓታል።

ለደህንነት ሲባልም የሞስኮው ትልቁ አየር ማረፊያ ለሰዓታት በረራዎችን አቋርጧል።

በአጸፋው ሩሲያ በዩክሬን ዋና ከተማ ኪቭ ላይ የባሊስቲክ ሚሳኤል ጥቃቶችን የሰነዘረች ሲሆን፤ በሱሚ ከተማ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት የአንድ ሰው ህይወት ማለፉ ተዘግቧል።

ቀደም ሲል ሩሲያ በኪቭ ባደረሰችው ጥቃት 1 ሺህ ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረ ታሪካዊ ገዳም ላይ ጉዳት ማድረሷ የአውሮፓ መሪዎችን ቁጣ መቀስቀሱ ይታወሳል፡፡

በዲፕሎማሲው ረገድ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በፈረንሳይ በተካሄደው የጂ7 ስብሰባ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት አድርገዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከውይይቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት ሁለቱም ወገኖች ስምምነት ላይ ለመድረስ ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት ሩሲያ በጦርነቱ ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወታደር እያጣች መሆኑን ገልጸዋል።

ሜሮን ገብሬ

ሰኔ 11/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *