አሜሪካ እና ኢራን በ60 ቀናት ውስጥ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል ስምምነት አደረጉ

በኳታር እና ፓኪስታን አደራዳሪነት በስዊዘርላንድ ሉሰርን ሀይቅ አቅራቢያ የተካሄደው የአሜሪካ እና ኢራን ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ንግግር በ60 ቀናት ውስጥ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ በመቅረጽ መጠናቀቁን አደራዳሪዎቹ አስታውቀዋል።

ይህ ስምምነት የተደረሰው የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ እና የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ መሀመድ ጋሊባፍ የመሩት ልዑክ ለ12 ሰዓታት ባደረጉት ጥብቅ ውይይት ነው።

ስምምነቱ ባለፈው ሳምንት የተፈረመውን ባለ 14 ነጥብ የማስታወሻ ሰነድ ተከትሎ የመጣ ቢሆንም፤ ቀጣዩ የቴክኒክ ድርድር ከፖለቲካዊ ስምምነቱ የበለጠ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል።

በጋራ መግለጫው መሰረት፤ ወታደራዊ ኦፕሬሽኖችን ለማስቆም የሚያግዝ የሊባኖስ ‹‹የግጭት መከላከያ ክፍል›› መቋቋሙ እና በስትራቴጂካዊው የሆርሙዝ ባህረ ሰላጤ ላይ የንግድ መርከቦች በሰላም እንዲያልፉ የሚያስችል የኮሙዩኒኬሽን መስመር መዘርጋቱ ዋና ዋና ስኬቶች ናቸው።

ይሁን እንጂ የኢራን የዩራኒየም ማበልጸግ ሂደት፣ የአሜሪካ ባለሙያዎች የኢራንን የኑክሌር ጣቢያዎች የመፈተሽ ስልጣን እና የማዕቀብ እፎይታ የጊዜ ሰሌዳ አሁንም ያልተቋጩ አወዛጋቢ ጉዳዮች ሆነው ቀጥለዋል።

በተጨማሪም እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ በፈጠረችው የጸጥታ ቀጣና ውስጥ ለመቆየት መፈለጓ እና የሄዝቦላህ ዝምታ ለስምምነቱ ተግባራዊነት ትልቅ ስጋት መሆናቸው ተገልጿል።

ሳራ ዮሐንስ

ሰኔ 15/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *