በደቡብ ኦስትሪያ ፊላኽ ከተማ የሚኖሩት ሩዶልፍ ሻውባኽ የተባሉ የፈጠራ ሰው፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ሲያዘጋጁት የቆዩትንና በጎችን ከተኩላ ጥቃት ይከላከላል የተባለለትን የሰንሰለት ካባ ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ በአርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ውዝግብ ተነስቷል።
በአገሪቱ እና በጎረቤት ጀርመን እየጨመረ የመጣውን የተኩላ ጥቃት ለመግታት ታስቦ የተዘጋጀው ይህ መከላከያ፣ በሹል እሾሃማ ነገሮች የተሸፈነ ቀላል የፕላስቲክ መረብ ሲሆን፣ እንስሳቱ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱና እንዲመገቡ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።
የፈጠራ ባለቤቱ ተኩላዎች ብልህ እንስሳት በመሆናቸው፣ በፈጠራው አማካኝነት ከሚደርስባቸው የሹል ካባው ሕመም በመነሳት ጥቃታቸውን እንደሚገቱ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
ሆኖም ከዘርፉ ባለሙያዎችና ከበግ አርቢዎች የተሰጠው ምላሽ በአብዛኛው አሉታዊ ሆኗል።
ተቺዎቹ እንደሚሉት፣ በመቶዎች ወይም በሺዎች የሚቆጠሩ እንስሳትን ይህን ካባ ማልበስ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅና በፋይናንስ ረገድ ዘላቂነት የሌለው መፍትሔ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ የበጉ ቆዳ ከመረቡ ጋር ተያይዞ ለእንስሳቱ ምቾት ማጣት ሊዳርግ እንደሚችል እና ተኩላዎችም ስልታቸውን በመቀየር እንደ ራስና እግር ያሉ ያልተሸፈኑ የሰውነት ክፍሎችን ሊያጠቁ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ጠቅሰዋል።
አቶ ሩዶልፍ ሻውባኽ የቀረቡትን ትችቶች በሙሉ ውድቅ ያደረጉ ሲሆን፣ ህዝቡ ሳይሞክረው በፎቶግራፍ ብቻ ፍርድ እየሰጠ ነው ሲሉ ተከራክረዋል።
ይሁን እንጂ በኦስትሪያ አልፕስ ተራሮች ላይ የተፈጠረውን ተቃውሞና ውዝግብ ተከትሎ፣ የፈጠራ ባለቤቱ ምርቱን እዚያ የመሞከር ሂደቱን ያቆሙ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአማራጭ አገራት የመስክ ፍተሻ ለማድረግ ምቹ ሁኔታዎችን በመፈለግ ላይ እንደሚገኝ ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል ።
ሐመረ ፍሬው
ሰኔ 17/2018 ዓ.ም
