በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በስፋት እየተስተዋለ የመጣው አስከፊ የመሬት መንሸራተት አደጋ የአየር ንብረት ለውጥ ቀጥተኛ ነጸብራቅ መሆኑ ተነገረ።

በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት እያደረሰ ያለው አስከፊ የመሬት መንሸራተት አደጋ፣ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ያመጣው ቀጥተኛ መዘዝ መሆኑ ተገለጠ።
 
የኢኮኖሚክስ፣ የአደጋ መከላከል እና የዘላቂ ልማት ባለሙያው ዶክተር አሸናፊ ኃይሉ ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ ለዚህ ተፈጥሯዊ መዛባት ዋነኛ ተጠያቂዎቹ ያደጉት ሀገራት ናቸው። እነዚህ ሀገራት በከፍተኛ መጠን ወደ ከባቢ አየር የሚለቁት የካርበን ዳይኦክሳይድ እና የግሪን ሃውስ ጋዞች የዓለምን ሙቀት እያናረው ይገኛል።
 
ባለሙያው አክለውም፤ «በብክለቱ ትርፍ ያጋበሱት ያደጉት ሀገራት ቢሆኑም፣ መርዛማው ጋዝ የሚያስከትለውን አስከፊ መቅሰፍት ግን እያስተናገዱ ያሉት እንደ እኛ ያሉ ታዳጊ ሀገራት ናቸው» ብለዋል።
 
ይህን የጉዳትና የሀብት አለመመጣጠን ለመቅረፍ ያደጉት ሀገራት ለታዳጊ ሀገራት የፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርጉበት ዓለም አቀፍ አሰራር መኖሩን ዶክተር አሸናፊ አስታውሰዋል። ታዳጊ ሀገራትም በበኩላቸው መጠነ-ሰፊ የዕፅዋት ተከላ በማካሄድ በከባቢ አየር ውስጥ ያለውን የካርበን መጠን የመቀነስ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
 
የዓለም ሙቀት መጨመር አሁን ላይ አስደንጋጅ  ደረጃ ላይ መድረሱን የገለጹት ዶክተር አሸናፊ፤ ከአደጋው ባሻገር እንደ ቆዳ ካንሰር እና የአተነፋፈስ ሥርዓት መዛባትን የመሰሉ ከባድ የጤና እክሎችን እያስከተለ መሆኑን አስገንዝበዋል።
 
ይህን ዘርፈ-ብዙ አደጋ ለመቋቋምም በስፋት ዕፅዋትን መትከልና በሳይንስ የተረጋገጡ የአየር ንብረት መከላከያ ዘዴዎችን በአግባቡ መጠቀም ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል፡፡

ሰላማዊት ዲታ

ሰኔ 18/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *