ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC) ዳኞች  ትራምፕ የጣሉባቸው ዕገዳ እና እርምጃዎች  ሕገ-ወጥ ናቸው አሉ።

ሦስት የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዳኞች ባለፈው ዓመት የተጣለባቸውን ማዕቀብ በመቃወም የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን እና አስተዳደራቸውን በመክሰስ ላይ ናቸው። ዳኞቹ የተጣለባቸው እርምጃ ሕገ-ወጥ ነው ሲሉ ይከራከራሉ።

እሮብ ዕለት በማንሃተን የፌደራል ፍርድ ቤት በገባው የክስ ማመልከቻ መሠረት፤ ካናዳዊቷ ዳኛ ኪምበርሊ ፕሮስት፣ ኡጋንዳዊቷ ሶሎሚ ባሉንጊ ቦሳ እና የቤኒን ተወላጇ ሬይን አደላይድ ሶፊ አላፒኒ-ጋንሱ ማዕቀቡ የተጣለው ዳኞችን ለመቅጣትና ለማስገደድ በማሰብ፣ ከሕግ አሠራር ውጭ የሆነ ጫና ለማሳደር ታቅዶ የተደረገ ነው ብለዋል።

የቁጥጥር ማዕቀቡ ባለፈው ዓመት በትራምፕ አስተዳደር በበርካታ የፍርድ ቤቱ ዳኞች ላይ የተጣለው፣ ፍርድ ቤቱ በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ላይ የእስር ማዘዣ በማውጣቱ እና ቀደም ሲል በአፍጋኒስታን ውስጥ የአሜሪካ ወታደሮች ፈጽመውታል የተባለውን የጦር ወንጀል ክስ ለመመርመር በወሰነው ውሳኔ ላይ ታይቶ በማይታወቅ የአጸፋ እርምጃ ነበር።

በማዕቀቡ ምክንያት ዳኞቹ በአሜሪካ የሚገኙ ንብረቶቻቸውና ሀብቶቻቸው እንዲታገዱ ተደርጓል። በተጨማሪም በአሜሪካ የሚገኙ ተቋማት “የገንዘብ፣ የዕቃዎች ወይም የአገልግሎቶች አቅርቦትን” ጨምሮ ከእነሱ ጋር ማንኛውንም የንግድ ልውውጥ እንዳያደርጉ ተከልክለዋል።

እ.ኤ.አ. በ2002 የተቋቋመው የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC)፤ በአባል አገራት ውስጥ ወይም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ጉዳዩ ሲመራለት በዘር ማጥፋት፣ በሰብአዊነት ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች እና በጦር ወንጀሎች ላይ ዓለም አቀፍ የዳኝነት ሥልጣን አለው።

ምንም እንኳን ፍርድ ቤቱ በ125 አባል አገራቱ ውስጥ በሚፈጸሙ የጦር ወንጀሎች፣ በሰብአዊነት ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች እና በዘር ማጥፋት ላይ የዳኝነት ሥልጣን ቢኖረውም፤ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያ እና እስራኤልን ጨምሮ አንዳንድ አገራት የፍርድ ቤቱን ሥልጣን አይቀበሉም።

በትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን፣ አስተዳደራቸው በፍርድ ቤቱ ከፍተኛ ዓቃቤ ሕግ ፋቱ ቤንሱዳ እና በአንድ ረዳታቸው ላይ ፍርድ ቤቱ በአፍጋኒስታን ላይ በሚያደርገው ሥራ ምክንያት ማዕቀብ ጥሎባቸው እንደነበር ይታወሳል ሲል አልጀዚራ ዘግቧል ።

ሰኔ 18/21018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *