ይህ የተገለፀው በዛሬው እለት በተከፈተው 8ኛውአግሮፉድእናፕላስትፕሪንትፓክዓለምአቀፍየንግድትርዒት ነው።
ከዚህ ኤግዚቢሽን ጋር ጎን ለጎን 2ኛው የኢትዮጵያ የምግብ ንግድ ትርዒት እና የኢትዮፒካ የቡና ንግድ ትርዒቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ።
በጀርመኑ ‘ፌርትሬድ መሴ’ (fairtrade Messe) እና በሀገር ውስጥ አጋሩ ‘ፕራና ኢቨንትስ’ ትብብር በተዘጋጀው በዚህ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ከ18 ሀገራት የተውጣጡ 1መቶ53 ተቋማት ምርትና አገልግሎታቸውን እያቀረቡ ይገኛሉ።
በኹነቱ ላይ ከጠንካራ የሀገር ውስጥ አምራቾች በተጨማሪ የብራዚል፣ ቻይና እና ጣሊያን ይፋዊ ተሳታፊዎች መካተታቸው ተገልጿል።
ይህም ለዘርፉ ባለሙያዎች ሰፊ የገበያና የቴክኖሎጂ ትስስር እንደሚፈጥር ተመልክቷል።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ኢትዮጵያ በ2026 የ9.2 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ በአፍሪካ ፈጣን ዕድገት የምታሳይ ሀገር እንደምትሆን መተንበዩን ተከትሎ የውጭ ኩባንያዎች በሀገሪቱ የኢንቨስትመንትና የንግድ ዘርፍ ላይ ያላቸው ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን የኤግዚቢሽኑ መከፈት ማሳያ መሆኑ ተገልጿል።
በንግድ ትርዒቱ ላይ ይፋ የተደረጉ የገበያ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ግብርና ለሀገሪቱ የሀገር ውስጥ ምርት 33 በመቶ ድርሻ ያለውና 66 በመቶ ለሚሆነው የሥራ ዕድል ፈጠራ ምክንያት የሆነ የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት ነው።
ሀገሪቱ በምግብ፣ መጠጥ እና ማሸጊያ ቴክኖሎጂ ላይ በዓመት እስከ 1መቶ71 ሚሊየን ዩሮ ኢንቨስት በማድረግ ከምስራቅ አፍሪካ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሆኗም ተመልክቷል።
በተጨማሪም የሀገሪቱ የፕላስቲክ ፍጆታ በዓመት በአማካይ የ11.5 በመቶ ዕድገት እያሳየ ሲሆን፥ኢትዮጵያ በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ሁለተኛዋ ትልቁ የፕላስቲክ ጥሬ ዕቃ አስመጪ መሆኗ ተነግሯል።
ይህ በሺህዎች የሚቆጠሩ የዘርፉን ባለሙያዎች ያገናኛል ተብሎ የሚጠበቀው ኤግዚቢሽን በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር እንዲሁም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ኤምባሲዎችና የንግድ ምክር ቤቶች ሙሉ ድጋፍ የተደረገለት ነው።
ከንግድ ትርዒቱ ጎን ለጎንም በኢትዮጵያ አምራቾች ማህበር አማካኝነት አዳዲስ መረጃዎችና እውቀቶች የሚሸመቱባቸው አስተማሪ የፓናል ውይይቶችና ጉባኤዎች እንደሚካሄዱ ታውቋል።
ሀና ሰይፉ
ሰኔ 18/2018 ዓ.ም
