በምክር ቤቱ የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ በቋሚ ኮሚቴው የተዘጋጀውን የጥናት ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
በሪፖርቱ ላይ ሰፊ ውይይት ያደረጉት የምክር ቤት አባላት፣ መረጃን ተደራሽ ከማድረግና ተጠያቂነትን ከማስፈን አንጻር የተለያዩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን ሰንዝረዋል።
አባላቱ ካነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል ጋዜጠኞች መታወቂያቸውን በማሳየት መረጃ እንዲያገኙ፣ እንዲሁም መረጃ ጠያቂዎች ሰነዶችን ለመገልበጥ (ፎቶ ኮፒ) የሚያስፈልገውን ወጪ ብቻ ከፍለው መረጃ እንዲያገኙ የሚገልጹ ድንጋጌዎች በሪፖርቱ ውስጥ በግልጽ ስለመካተታቸው ማብራሪያ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም የሀገርን ሚስጥራዊ መረጃ አሳልፈው በሚሰጡ አካላት ላይ የተጣለው ቅጣት አነስተኛ መሆኑን በመጥቀስ የቅጣቱ መጠን እንዲፈተሽ ጠይቀዋል።
ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት አቶ እውነቱ አለነ፣ አዋጁ ጋዜጠኞች ለሕዝብ ጥቅም የሚውሉ መረጃዎችን ያለምንም ክፍያ ማግኘት እንደሚችሉና ሌሎች መረጃ ጠያቂዎች ደግሞ ለሰነድ ማባዣ የሚሆን አነስተኛ ወጪን ብቻ ሸፍነው መረጃ ማግኘት እንዲችሉ እንደሚፈቅድ ገልጸዋል።
የሀገር ሚስጥር አሳልፎ ከመስጠት ጋር በተያያዘ ለቀረበው የቅጣት ጥያቄም ሰብሳቢው ሲያስረዱ፤ በአዋጁ የተጠቀሱት ቅጣቶች በወንጀል ሕጉ ውስጥ ያልተካተቱ ጥፋቶችን ብቻ የሚመለከቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ከባድ የሆኑ የሀገር ደኅንነትና የሚስጥር ጥሰቶች ግን በቀጥታ በሀገሪቱ የወንጀል ሕግ መሠረት ተጠያቂነትን እንደሚያስከትሉ አብራርተዋል።
ምክር ቤቱም የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ ከመረመረ በኋላ፣ የመረጃ ነጻነት ረቂቅ አዋጅን “አዋጅ ቁጥር 1427/2018” አድርጎ በሙሉ ድምፅ አጽድቆታል።
ሰኔ 18/2018 ዓ.ም
