በደቡብ አፍሪካ ፀረ-ስደተኛ ተቃውሞዎች ወደ ሁከት ሊቀየሩ ይችላሉ ከሚል ስጋት ከፍተኛ የፀጥታ ኃይል ተሰማራ

ብዙዎች ከሁከትና ከጥቃት ለማምለጥ አስቀድመው ከአገሪቱ ተሰደዋል። የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ እስካሁን 25,000 የሚሆኑ ስደተኞች ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ገልጿል። አብዛኞቹ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት የመጡ ናቸው።
 
ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በተቃውሞው ላይ ለመሳተፍ ያቀዱ ወገኖች ያለምንም “ማስፈራሪያ፣ ዛቻ ወይም የአስቸኳይ ጊዜ ማስጠንቀቂያ ” ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲያደርጉት አሳስበዋል።
 
የታቀዱት ተቃውሞዎች፣ ዘመቻ አድራጊዎች ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው የውጭ አገር ዜጎች በሙሉ ከአገር እንዲወጡ ያስቀመጡትን መደበኛ ያልሆነ የጊዜ ገደብ የሚያመለክቱ ናቸው።
 
ሕጋዊ ሰነድ የሌለው አንድ የማላዊ ዜጋ ለቢቢሲ እንደተናገረው “ወደ አገሩ በመመለሱ ደስተኛ” ቢሆንም፣ አራት ታዳጊ ልጆቹን ጥሎ በመሄዱ ግን “ልቡ እንደተሰበረ” ገልጿል።
 
ከተቃውሞዎቹ አንዱ የታቀደባት ጆሃንስበርግ ከተማ ባልተለመደ ሁኔታ ፀጥ ብላለች።
 
ሰልፈኞቹ ይሰበሰቡባቸዋል ተብለው በሚጠበቁባቸው አካባቢዎች ያሉ ሱቆች በሙሉ የተዘጉ ሲሆን፣ በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይም ከፍተኛ የፖሊስ ቁጥጥር ይታያል።
 
ፖሊስ እንደገለጸው ከሆነ በጆሃንስበርግ ትልቁ የከተማ መንደር (ታውንሺፕ) በሆነው ሶዌቶ ውስጥ የውጭ ዜጋ ንብረት የሆነን ሱቅ ዘርፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ አምስት ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
 
በተጨማሪም በኳዙሉ-ናታል ግዛት በሀማርስዴል አካባቢ በሚገኝ አንድ አነስተኛ ሱቅ ሰብረው በመግባት የተጠረጠሩ አምስት ሰዎች ተይዘዋል። በዚሁ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው በደርባን መሃል ከተማ የሚገኙ በርካታ የንግድ ተቋማት ተዘግተዋል።
 
ራማፎሳ ተቃዋሚዎች በሰላማዊ እና በኃላፊነት ስሜት እንዲንቀሳቀሱ በተደጋጋሚ ያስጠነቀቁ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የስደተኞች ህግ ማሻሻያ እንደሚያስፈልግ አምነዋል።
 
በሳምንታዊ የዜና መጽሔታቸው ላይ ለዜጎች ባስተላለፉት መልዕክት “በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ አንዳንድ የውጭ አገር ዜጎች እዚህ ያሉት በሕጋዊ መንገድ ነው” በማለት አሳስበዋል።
 
“እነሱ ይሰራሉ፣ ይማራሉ፣ ቤተሰብ ይመሰርታሉ፣ በኢኮኖሚያችን ላይ መዋዕለ ንዋይ ያፈሳሉ እንዲሁም ለህብረተሰባችን አዎንታዊ አስተዋፅዖ ያበረክታሉ። እነሱም ቢሆኑ በሕጎቻችን እና በሕገ-መንግስታችን የመጠበቅ መብት አላቸው።”
 
“የመቃወም መብት እና የመናገር ነፃነት ሰዎችን ለማስፈራራት ወይም ለማሸበር፣ ወይም ደግሞ በንብረት ውድመትና በሁከት ድርጊቶች ላይ ለመሳተፍ ፈቃድ አይሰጥም” ሲሉ ጽፈዋል።
 
እንደ ኦፊሴላዊ መረጃዎች ከሆነ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሕጋዊ ሰነድ ያላቸው የውጭ አገር ዜጎች ይኖራሉ።
 
የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ከመድረሱ በፊት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ለደህንነታቸው በመስጋት በጊዜያዊ ካምፖች ውስጥ ጉዳያቸው እስኪታይ ድረስ ለበርካታ ሳምንታት ሲጠባበቁ ቆይተዋል።
 
ሰኔ 23/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *