የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ቶማስ እሸቴ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ፤የክረምት ወቅት መግባቱን ተከትሎ የወንጀል ድርጊቶች ሊጨምሩ እንደሚችሉ ገልጸዋል።
በክረምት ወቅት የሰዎች እንቅስቃሴ የሚገደብ በመሆኑ፤ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ወንጀለኞች ስርቆትና መሰል ድርጊቶችን ሊፈጽሙ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።
በተለይም የመኖሪያ ቤት ሰብሮ መግባትና የቤት ውስጥ ንብረቶችን የመስረቅ ወንጀሎች በዚህ ወቅት ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ኮማንደሩ አስረድተዋል።
ከመኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ በተለያዩ ተቋማትና መጋዘኖች ላይ ያነጣጠሩ የስርቆት ድርጊቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ በመረዳት ተገቢው ጥበቃ ሊደረግ እንደሚገባ ገልፀዋል።
በተጨማሪም የተሽከርካሪዎች መለዋወጫ ዕቃዎችን መዝረፍና ከተሽከርካሪ ውስጥ ንብረቶችን መስረቅ በክረምት ወቅት በስፋት የሚታዩ የወንጀል አይነቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
እነዚህን የወንጀል ድርጊቶች ለመከላከል ፖሊስ ከማህበረሰቡና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ተመላክቷል።
ፖሊስ ወንጀልን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ለዚህም የህዝቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ኮማንደር ቶማስ አፅንኦት ሰጥተዉ ተናግረዋል ።
ሊዲያ ደሳለኝ
ሐምሌ 17/2018 ዓ.ም
