በማህበረሰቡ ዘንድ የሚነሳውን የቡና ጣዕም መለወጥና የጥራት መጉደል ቅሬታዎችን ለመፍታት በጥራት ማሻሻል ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል ያሉት የቡናና ሻይ ባለስልጣን የዋና ዳይሬክተር ፅህፈት ቤት ሀላፊ ዶ/ር ሰፊሳ አባቡ ናቸው።
ጥራትን ለማስጠበቅ እና የቡና ጥራትን ከተቀመጠው ደረጃ በታች የሚያወርዱ አሰራሮችን ለማስቀረት የባለስልጣኑ ባለሙያዎች ወደ አምራቾች ዘንድ በአካል በመሄድ በምርት አሰባሰብና ዝግጅት ሂደት ላይ አስፈላጊውን ማሳሰቢያና ክትትል እያደረጉ ይገኛል ብለዋል፡፡
እንዲሁም ደግሞ ቡና ከለቀማ ጀምሮ በምድር ላይ እንዳይሰጣና የጥራት ደረጃው በተጠበቀ አልጋ ላይ ብቻ እንዲሰጣ የማድረግ ጥብቅ መመሪያ እየተተገበረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በጥራት መጉደልና ባልተገባ መንገድ በሚካሄዱ የማቀናበር ሂደቶች ላይ የሚሳተፉ አካላትን በህግ የመጠየቅና የቁጥጥር ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን አንስተዋል፡፡
በገበያው ላይ የነበረውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ከመሸጫ ጊዜው በፊት ከአምራቾችና ከገዢዎች ጋር የግንዛቤ ፈጠራና የማስጠንቀቂያ መልዕክቶች መተላለፋቸውን ያነሱት ሀላፊው፤ በገዢዎች መካከል የሚደረጉ አላስፈላጊ የሽሚያ ምክንያቶች የዋጋ ጭማሪ እንዲኖር እያደረጉ መሆናቸውን አክለዋል፡፡
ሀና ሰይፉ
ሐምሌ 17/2018 ዓ.ም
