ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ እና ንብ ኢንሹራንስ በጋራ በመሆን በእንጦጦ ተራራ በሚገኘው እና በባንኩ ስም በተከለለው የሀገር በቀል ችግኝ መትከያ ስፍራ ባዘጋጁት የአረንጓዴ አሻራ አካል በሆነው አመታዊ የሀገር በቀል ችግኝ መትከል መርሀ ግብር ላይ እጽዋትን በመትከል እና በመንከባከብ አከባቢን ከመጠበቅ ባለፈ የተፈጥሮ አደጋን አስቀድሞ መከላከል እንደሚቻል የንብ ኢንሹራንስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ዙፋን አበበ ተናግረዋል፡፡
ስራ አስፈጻሚዋ እንደገለፁት፤ ንብ ኢንሹራንስ በዋናነት አደጋ ከተከሰተ በኋላ ዋስትና የመስጠት ስራ የሚሰራ ሲሆን፤እንደ ችግኝ ተከላ ያሉ ማህበራዊ ሀላፊነቶችን መወጣት አና አስቀድሞ አከባቢን መጠበቅ ደግሞ የተፈጥሮ አደጋን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
መርሀ ግብሩን አስመልክቶ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሄኖክ ከበደ ባስተላለፋት መልዕክት፤ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ከአከባቢ ጥበቃ ጋር የተሳሰረ ሲሆን፤ በቀደሙት አመታት የተተከሉት ችግኞች በተደረገላቸው እንክብካቤ በተሳካ ሁኔታ መጽደቅ መቻላቸውን አንስተዋል፡፡
አቶ ሄኖክ አክለውም ባንኩ ይህንን እና መሰል የአከባቢ ጥበቃ ተግባራትን በቀጣይ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
በመርሀ ግብሩ ላይ የተሳተፉት የባንኩ ሰራተኞች ለኢትዮ ኤፍኤም እንደተናገሩት፤ እንደ ባህር ዛፍ ያሉ ችግኞችን በመቀነስ አገር በቀል የሆኑ ችግኞችን መትከል መቻሉ የተፈጥሮ ሚዛንን በመጠበቅ ረገድ ሚናው የላቀ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
ሰላማዊት ዲታ
ሐምሌ 20/2018 ዓ.ም
