የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ዘመናዊና ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችልና እ.ኤ.አ እስከ 2049 የሚዘልቅ የ25 ዓመታት የኃይል ማከፋፈያ ሥርዓት ማስፋፊያና ማሻሻያ ማስተር ፕላን ይፋ አደረገ።
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው በማስተር ፕላኑ የምክክር መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኤሌክትሪክ ለኢንዱስትሪ፣ ለዲጂታል ሽግግር፣ ለግብርናና ለሌሎች ማህበራዊ ዘርፎች እድገት መሠረት በመሆኑ ይህ ፍኖተ ካርታ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅት 5,453 ሜጋ ዋት አካባቢ የደረሰው የሀገሪቱ ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት እ.ኤ.አ እስከ 2049 ድረስ በሰባት እጥፍ በማደግ 40,000 ሜጋ ዋት ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህን ፍላጎት ለማሟላትም የማከፋፈያ ኔትዎርኩን በቴክኖሎጂ ማዘመን የግድ መሆኑን ገልጸዋል።
ማስተር ፕላኑ የአገልግሎት አሰጣጡን ከባህላዊ አሠራር ወደ ስማርት ግሪድ ወይም ዘመናዊ ኔትዎርክ ለመቀየር ያለመ ነው ተብሏል።
ይህም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI)፣ በዘመናዊ የኃይል ቆጣሪዎች (Smart Meters) እና አስተማማኝ የሳይበር ደህንነት ላይ የተመሠረተ እንደሚሆን ተጠቁሟል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
ለዚህ ግዙፍ የ25 ዓመታት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ 30.65 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ኢንቨስትመንት እንደሚያስፈልግ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም 84 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ለሀገሪቱ እንደሚያስገኝ ተጠቁሟል።
“ለእያንዳንዱ ለሚወጣ 1 ዶላር፣ 3 ዶላር የሚሆን የኢኮኖሚ ጥቅም ይገኛል” ያሉት ኢንጂነር ጌቱ፣ ኢንቨስትመንቱ ከፍተኛ የሥራ ዕድልና ብልጽግናን እንደሚያመጣ አስረድተዋል።
ከማስተር ፕላኑ ዝግጅት ጎን ለጎን ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መሐንዲሶች የዕውቀት ሽግግርና ሥልጠና መሰጠቱ እንደ ትልቅ ስኬት ተጠቅሷል። ዋና ሥራ አስፈፃሚው ለዓለም ባንክና ለኢራኑ ሞኔንኮ (Monenco Iran) አማካሪ ድርጅት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
“ዛሬ ማቀድ፣ ነገን ማብቃት” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ይህ ማስተር ፕላን፣ የኢትዮጵያን የኃይል ዘርፍ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግርና ለዜጎች ፍትሃዊ የኃይል ተደራሽነትን እንደሚያረጋግጥ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው ገልፀዋል።
አዲስዓለም አበበ
ሐምሌ 20/2018 ዓ.ም
