በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች እና ጦርነቶች ለጤና አገልግሎቱ ችግር መሆናቸውን ጤና ሚኒስቴር ነው ያስታወቀው።
በተለይም የእናቶች እና ህፃናት ጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ እንቅፋት መፍጠራቸውን በጤና ሚኒስቴር የስነ-ተዋልዶ ጤና ቤተሰብ ዕቅድና የአፍላ ወጣቶች ፕሮግራም ኃላፊ ዶ/ር አለማየሁ ሁንዱማ ገልፀዋል።
በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የነበረው ጦርነትና አሁን ላይ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶች የጤና ባለሙያዎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው አገልግሎት እንዳይሰጡ ከማድረጋቸውም በላይ የግብዓትና የነዳጅ እጥረት እንዲከሰት ምክንያት መሆናቸውን አንስተዋል።
ዶክተር አለማየሁ እንዳሉት፥ ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች እናቶች ለሞትና ለከፍተኛ ስቃይ የሚዳረጉበት ዕድል ሰፊ በመሆኑ፥መንግስት ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በተንቀሳቃሽ የጤና ቡድኖች አማካኝነት ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ ይገኛል።
በቀጣይም አገልግሎቱ ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ ከአካባቢው አስተዳደሮች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
ሊዲያ ደሳለኝ
ሐምሌ 20/2018 ዓ.ም
