እየተካሄደ በሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ እስካሁን የተወሰነ ነገር አለመኖሩን የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የምክከሩን የእስካሁን ሂደት በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም ላለፉት ሁለት ቀናት አራት ሺህ ተሳታፊዎች በጥቃቅን ቡድን ተከፋፍለው(በ50 ቡድን) አስር አስር በመሆን በተሰጣቸው አጀንዳዎች ላይ ሲመክሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
የመከሩባቸው ጉዳዮችም እየተሰነዱ መሆኑንና ተመካካሪዎች የሚያቀርቧቸው ሃሳቦች በሚገባ እየተሰነዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመጀመሪያው የምክከር ሂደት(የጥቃቅን ቡድን) ወደ ንዑስ ቡድን ተሻጋግሮ በሚገባ ምክክር እንደሚደረግም ዋና ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል፡፡
በምክክሩ ሁሉም ተመካካሪዎች ሃሳባቸውን በነጻነት እና በግልጽ እያቀረቡ እንደሚገኙ ገልጸው እስካሁን ያለቀና የተወሰነ ነገር አለመኖሩን አብራርተዋል፡፡
ሀሳቦች እየተቀራረቡ ቢሆንም ነገር ግን ውሳኔ የሚቀርብበት ምዕራፍ ላይ ገና አልተደረሰም ሲሉም አስታውቀዋል፡፡
የፊታችን ሰኞ የ2መቶ50ዎቹ (ስልታዊ ቡድን) ምዕራፍ ተጠናቆ ወደ 500ዎቹ እንሸጋገራለን የሚል እምነት እንዳላቸውም ዋና ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ጠቁመዋል፡፡
የኮሚሽኑ ዓላማ ሁሉም በእኩልነት እንዲነጋገር መሆኑን ጠቁመውም የምክክሩ ስነ ዘዴ ሁሉም እኩል አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ሐምሌ 21/2018 ዓ.ም
