ቻድ ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለመውጣት ማቀዷን አስታወቀች

ቻድ ከቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ፣ ኒጀር እና ቬንዙዌላ በመቀጠል ፍርድ ቤቱን የመልቀቅ ሂደቱን እንደምትጀምር መግለጿ፣ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ሌላው ተጨማሪ ስጋት ሆኗል።

የቻድ መንግሥት ባወጣው መግለጫ፤የፍርድ ቤቱ ውጤታማነት ‹‹ውስን እና ያልተመጣጠነ›› መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤መቀመጫውን በሄግ ያደረገው ተቋም ትኩረቱን በአፍሪካ አገራት ላይ ብቻ ያደርጋል ሲል ከሷል።

መግለጫው ‹‹ፍርድ ቤቱ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ሰባት ሰዎች ብቻ ሲሆኑ፣ ከእነዚህም መካከል ስድስቱ በአፍሪካ ጉዳዮች ክስ የተመሰረተባቸው ናቸው›› ብሏል።

ይህ የተገለጸዉ፤ቻድ በጎረቤት አገር ሱዳን በሠራዊቱ እና በከፊል ወታደራዊ ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ውስጥ እጇ አለበት የሚል ጥርጣሬ ባለበት ወቅት ነው።

ባለፈው ሳምንት የቻድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የፌስቡክ ገጽ፣ አሜሪካ ቻድ የICC አባልነቷን ድጋሚ እንድታስብ ግፊት እያደረገችባት መሆኑን አስፍሮ ነበር።

ሆኖም ሚኒስትሩ በኋላ ላይ አሜሪካ ከውሳኔው በስተጀርባ መሆኗን ያስተባበሉ ሲሆን፤ ይልቁንም ቻድ ‹‹ፍርድ ቤቱ በአሁኑ ጊዜ ከሚሠራበት መንገድ ጋር አብራ መጓዝ አልቻለችም›› ሲሉ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ግለሰቦችን በጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች በሕግ ይጠይቃል።

ሀና ሰይፉ

ሐምሌ 21/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *