በአሰላ ከተማ በ15 ሚሊዮን ብር ወጪ ለሴት ተማሪዎች የተገነቡ ዘመናዊ “አስተማማኝ የመቆያ ስፍራዎች” ተመረቁ

በአርሲ ዞን አሰላ ከተማ በሚገኙ ሁለት አንጋፋ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሴት ተማሪዎች ሁለንተናዊ
ድጋፍ የሚሰጡ “አስተማማኝ የመቆያ ስፍራዎች” (Safe Spaces) ተገንብተው በዛሬ እለት በይፋ ተመርጠዋል።

በአሰላ ከተማ አስተዳደር፣ በኦዳ እና በጭላሎ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተገነቡት እነዚህ ስፍራዎች፤ ‘እሸት
የህፃናትና ወጣቶች ልማት ድርጅት’ (Child & Youth Development Organization) ባወጣው 15 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ኢንቨስትመንት የተገነቡ ናቸው።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ታረቀኝ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቶቹ በጥራትና በአጭር ጊዜ (በሁለት ወራት ውስጥ) ተጠናቀው ለአገልግሎት የበቁ ሲሆን፣ ከ4 ሺህ በላይ ሴት ተማሪዎችን በቀጥታ ተጠቃሚ ያደርጋሉ።

“ግንባታው ተማሪዎቹ በትምህርት ገበታቸው ላይ ውጤታማ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ባለፈ፣ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ተማሪዎችን በውሳኔ ሰጪነት፣ በስልጠና እና በሜንተርሺፕ የማብቃት ስራዎች በዚሁ ማእከል ውስጥ ይከናወናሉ” ብለዋል አቶ ሲሳይ።

የአሰላ ከተማ ከንቲባ አቶ ፀጋዬ በጅጋ በምረቃው ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ድርጅቱ ቀደም ሲል በስሊንጎት ትምህርት ቤት ተመሳሳይ ስራ ማከናወኑን አስታውሰው፣ አሁን ደግሞ የ80 ዓመታት እድሜ ባለው አንጋፋው ጭላሎ ትምህርት ቤት እና በኦዳ ትምህርት ቤት
ላከናወነው ተግባር ምስጋና አቅርበዋል።

ከንቲባው አያይዘውም፣ ይህ ትምህርት ነክ ልማት ከተማዋ ከጀመረቻቸው ታላላቅ የመሰረተ ልማት ስራዎች ጋር የተቆራኘ መሆኑን ገልጸዋል።

አሰላን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ የወንዞች ልማት፣ የ18 ሚሊዮን ብሩ የ”ቡርቂቶ ፓርክ” ግንባታ፣
የአርዱ አይቅ ልማት፣ እንዲሁም አዳዲስ የአስፋልት መንገዶችና የጤና ተቋማት ግንባታ ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመዋል።

አሰላ የብሄር ብሄረሰቦች መኖሪያና የሰላም አምባሳደር በመሆኗ “ታዳጊዋ ኢትዮጵያ” የሚል ስያሜ እንደተሰጣት የጠቀሱት ከንቲባው፣የዛሬው የሴት ተማሪዎች መቆያ ስፍራ ምረቃም የከተማዋን የነገ ተስፋዎች ለማብቃት ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል።

ልዑል ወልዴ

ሐምሌ 23/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *