በአዲስ አበባ ኮንቬንሽን ሴንተር ከነሀሴ 21 እስከ ጳጉሜ 05 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ “አደይ አዲስ ዓመት ታላቅ የንግድ ኤክስፖና ፌስቲቫል” ሊዘጋጅ መሆኑ ተገለጸ።
ዝግጅቱን “ማስተር ፒስ ትሬዲንግ” እና “ራይት ኢቨንት” ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅታቸውን አጠናቀው የንግድ ማህበረሰቡን በመመዝገብ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ የሚዘጋጀው ይህ ኤክስፖ፤ ሸማቹ ህብረተሰብ ያለ አላስፈላጊ የጉዞ ወጪ እና እንግልት ጥራት ያላቸው ምርቶችና አገልግሎቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ለማስቻል ያለመ መሆኑ ተመላክቷል። አዘጋጆቹ ለነጋዴዎች የቦታ ክራይ እስከአሁን ካሉት መሰል መድረኮች በቀነሰ መልኩ እንደሚያቀርቡም ተገልጿል።
የኮንቬንሽን ሴንተሩ በሰሚት አካባቢ መገኘቱ ከሰሚት፣ ከአያት፣ ከአራብሳ፣ ከየካ አባዶ እና ከኮተቤ የሚመጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በቅርብ ርቀት ግብይት እንዲፈጽሙ ትልቅ ምቾት እንደሚፈጥርላቸው ተጠቁሟል። በሺዎች የሚቆጠሩ መኪናዎችን ማስተናገድ የሚችለው ይህ ስፍራ፣ በቀን ከ10 ሺህ በላይ ጎብኝዎችን ይስባል ተብሎ ይጠበቃል።
ከንግድና ግብይት ባሻገር ከ200 በላይ አምራቾች፣ አስመጪዎች እና አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚሳተፉበት መድረክ መሆኑ ተገልጿል። በ15ቱ ቀናት ቆይታም ከአንጋፋ አርቲስቶች ጋር የሚቀርቡ የሙዚቃ ድግሶች፣ ፋሽን ትርኢቶች፣ የስታንድአፕ ኮሜዲዎች እና ከ8,000 በላይ ታዳሚዎችን የሚጠብቅ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ኮንሰርት ይካተታሉ ተብሏል።
ፌስቲቫሉ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ሰፋ ያለ የመጻህፍት አውደ ርዕይ፣ የመጻህፍት ልገሳ እና የበጎ አድራጎት ስራዎችን አካቶ እንደሚይዝ ተነግሯል። አዲስ አበባን እና ኢትዮጵያን በንግድ፣ በባህልና በቱሪዝም ለማስተዋወቅ ታስቦ የተዘጋጀው ይህ ሁነት አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያካተተ ነው።
ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀው ኮንቬንሽን ሴንተር በዓልን ምክንያት አድርጎ ሲዘጋጅበት ይህ የመጀመሪያው መሆኑ ታይቷል። አዘጋጆቹ ከማዘጋጃ ቤቱ አስተዳደር፣ ከደህንነትና ጸጥታ አካላት እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸው፣ የዘመን መለወጫ በዓልን በድምቀት ለማክበር ዝግጅቱ መጠናቀቁን አረጋግጠዋል።
አቤል እስጢፋኖስ
ሐምሌ 23/2018 ዓ.ም
