የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የደረጃ “ለ “ግብር ከፋዮች በዘንድሮ በጀት ዓመት 9.2 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅጃለሁ ብሏል
ቢሮዉ በዛሬዉ እለት በሰጠዉ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገረዉ 4 መቶ 56 ሺህ ከሆኑት የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዩች ነዉ ይህንን ለመሰብሰብ ያቀድኩት ሲል ገልፆል።
የቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አቶ ሰዉነት አየለ መረጃ ለተሟላላቸዉ ግብር ከፋዩች የግብር ዉሳኔ በስልካቸው እንዲደርስ እያደረግነዉ ሲሉ ተናግረዋል።
እስከ ሀምሌ 25 ድረስ የግብር ዉሳኔ የደረሳቸዉ ግብር ከፋዩች ዓመታዊ ግብራቸዉን እስከ ሀምሌ 30/2018 ዓ.ም ድረስ የግብሩን ኦንላይን እንዲከፍሉ ቢሮዉ አሳስቧል።
የደረጃ ለ ግብር ከፋዮች በተሸሻለው የገቢ ግብር አዋጅ መሰረት የግብር ግዴታቸውን ከሐምሌ 1 እስከ ሐምሌ 30/2018ዓ.ም መክፈል ይጠበቅባቸዋል።
ቢሮዉ ቀነ ገደቡን ጠብቀዉ ባልከፈሉ ግብር ከፋዩች ቅጣትና ወለድ እንደሚጠብቃቸዉም ገልጿል።
ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች ከቢሮዉ የግብር ዉሳኔ መልእክት በስልካቸው ያልደረሳቸዉ ግብር ከፋዩች እስከ ነሀሴ 20 ባለዉ ጊዜ ያለ ቅጣት አመታዊ ግብራቸዉን መክፈል እንደሚችሉ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በሰጠዉ መግለጫ ጠቅሷል።
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በ2019 በጀት አመት 3 መቶ 80 ቢሊዮን ብር የመሰብሰብ ዕቅድን እንዳለዉ ገልጿል።
በመዲናይቱ በንግድ ትርፍ፣ በኪራይና በራይድ የንግድ ዘርፎች የተሰማሩና በግብር ስርዓት ውስጥ ያሉ 456 ሺህ የደረጃ” ለ” ግብር ክፋዮች አሉኝ ብሏል።
ቁምነገር አየለ
ሐምሌ 29/2018 ዓ.ም
