ኢትዮጵያ ከገጠሟት ውስብስብና ዘመን ተሻጋሪ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ቀውሶች ለመውጣት አሁን የተጀመረው ብሔራዊ የምክክር ሂደት ታሪካዊና ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን የዳያስፖራ አባላት ገለጹ።
ተሳታፊዎቹ አገሪቱ ፈተናዎቿን በጠመንጃ ሳይሆን በሠለጠነ የውይይት ባህል ለመፍታት መነሳቷ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለሂደቱ ስኬትና ለአገሪቱ መረጋጋት የሕግ የበላይነት መረጋገጥ ዋናው መሠረት መሆኑን በአጽንኦት አሳስበዋል።
ከዩናይትድ ኪንግደም የመጡት ዶክተር ነቢዩ ገሰሰ በሂደቱ ውስጥ የሕግ የበላይነት ሊኖረው ስለሚገባው ሚና ሲያስረዱ፦ “የሕግ የበላይነት ላይ ከተስማማን ሁሉም ሰው እኩል ሜዳ ላይ ይጫወታል።
ልዩነቶችና ቅሬታዎች ካሉን መጥተን በሠለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ እንቀመጣለን፤ እንወያያለን፤ ጥያቄ እናቀርባለን፤ መልስ እንሰጣለን፤ እንቀበላለን። መንገዱ እሱ ነው” ብለዋል። ሁሉም ዜጋ እኩል የሚስተናገድበት የፍትሕ ሥርዓት ካልሰፈነ የምክክሩ ውጤት ዘላቂ ሊሆን እንደማይችልም ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ ከካናዳ የመጡት አቶ ዳንኤል ሆርዶፋ፣ የምክክር መድረኩ ኢትዮጵያውያን በነጻነት፣ በፍትሕና በእኩልነት የሚኖሩባትን አገር ለመገንባት የተገኘ ወርቃማ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸው፤ እያንዳንዱ ዜጋ ለሂደቱ ስኬት በበጎ መንፈስ ሊቆም እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
የሰላምና ደኅንነት ባለሙያው አቶ ልዑልሰገድ አበበ በበኩላቸው፣ ከዚህ ታላቅ አገራዊ ምክክር የሚጠበቁ የውሳኔ ሃሳቦች ለታላላቅ አገራዊ ማሻሻያዎች በር እንደሚከፍቱ ገልጸዋል። በተለይም ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያዎችን ለማድረግና እውነተኛ አገራዊ እርቅን ለማውረድ ሂደቱ መነሻ እንደሚሆን አመልክተዋል።
በአጠቃላይ የዳያስፖራ አባላቱ ብሔራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ብቸኛው ዋስትና መሆኑን ገልጸው፤ ሂደቱ በሕዝብ ዘንድ አመኔታን እንዲያተርፍና ዲሞክራሲያዊ እሴቶችን እንዲያጎለብት የሁሉም ወገኖች ቅን ልቦናና ንቁ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
ልዑል ወልዴ
ነሐሴ 05/2018 ዓ.ም
“የሕግ የበላይነትና የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ብቸኛው አማራጭ ነው” — የዳያስፖራ ተወካዮች
