የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዲጂታል የባንክ አገልግሎት ላይ የሚታዩ የሳይበር ደህንነት ስጋቶችን ለመከላከልና በዘርፉ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ፣ በመጪው ጥቅምት ወር 2019 ዓ.ም 3ኛውን የመረጃ ደህንነት ግንዛቤ ማስጨበጫ ወር (Cyber Security Awareness Month) እንደሚያከብር አስታውቋል።
ባንኩ ዘንድሮ ዝግጅቱን የሚያከናውነው አህጉራዊ ተሞክሮ ካለው ሲአይኦ አፍሪካ (CIO Africa) ከተሰኘ ተቋም ጋር በመተባበር እንደሆነ ገልጿል።
የባንኩ የመረጃ ሥርዓት ደህንነት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ስዩም ዳምጠው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከቱት፣ ይህ የሳይበር ደህንነት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ23ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ለ7ኛ ጊዜ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደረጃ ደግሞ ለ3ኛ ጊዜ የሚከበር ነው።
ዝግጅቱ “ባንኩ የጀመረውን የሳይበር ጥቃትን የመከላከል ብቃት የማጠናከር ስራ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግርና ከሀገሪቱ የዲጂታል ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ጋር የተጣጣመ ነው” ብለዋል።
በጥቅምት ወር 2019 ዓ.ም በሚከበረው በዚህ መርሃ ግብር አራት ዋና ዋና ግቦች የተቀመጡ ሲሆን፣ ለሰራተኞችና ደንበኞች ግንዛቤ መፍጠር፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ትብብር መፍጠር፣ አዳዲስ ስጋቶችን መለየት እና ዓለም አቀፍ የደህንነት ማዕቀፎችን መተግበር እንደሆኑ ተገልጿል።
የሲአይኦ አፍሪካ (CIO Africa) ዳይሬክተር ሚስተር አንደሪው ካራንጃ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሀገሪቱ የዲጂታል ሽግግር ውስጥ እያከናወነ ያለውን ሚና አድንቀዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት የባንኩ የፋይናንስ ግብይቶች በዲጂታል መንገድ እየተከናወኑ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ጠንካራ የዲጂታል ሥነ-ምህዳር ለመፍጠር ባንኩ ከሲአይኦ አፍሪካ ጋር በጋራ መስራቱ ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
አዲስዓለም አበበ
ነሐሴ 05/2018 ዓ.ም
