በቻይና ሁናን ግዛት «አቶ ሲ» የተባለ ግለሰብ ሰክሮ በማሽከርከሩ ምክንያት የሚጠበቅበትን የሕግ ተጠያቂነት ለማምለጥ ሲል ከቤተሰቡ ጋር በመተባበር የሐሰት የሞት እና የቀብር ሥነ-ሥርዓት መፈጸሙን ፖሊስ ይፋ ባደረገው መረጃ ገልጿል።
ግለሰቡ ቀደም ሲል ያለ መንጃ ፈቃድ በስካር በማሽከርከር ሁለት ጊዜ የተያዘ ሲሆን፣ ለሦስተኛ ጊዜ በተመሳሳይ ጥፋት በመያዙ ምክንያት የሚጠብቀውን የእስራት ቅጣት በመፍራት በዋስ ከተለቀቀ በኋላ ከሀገር ለማምለጥ አቅዷል። በመቀጠልም አቶ ሲ እና ቤተሰቦቹ አስቀድመው የሬሳ ሣጥን በመግዛት ዕቅዳቸውን መተግበር ጀምረዋል።
ፖሊስ እንዳወጣው መረጃ፤ አቶ ሲ በመድኃኒት መጠን ማለፍ (Overdose) ምክንያት እንደሞተ ለማስመሰል ባዶ የመድኃኒት ብልቃጦችን በቤቱ በመበተን፣ እስትንፋስን የመያዝ ልምምድ በማድረግ እና የሰውነት ሙቀትን የሚቀንሱ መሣሪያዎችን በመጠቀም የሐሰት ሞቱን አስመስሏል።
የቀብር ሥነ-ሥርዓቱ በተካሄደበት ዕለትም እናቱ እና አያቱ «የአቶ ሲ ፊት በመድኃኒቱ ምክንያት ተበላሽቷል» የሚል ምክንያት በመስጠት ፊቱን በጨርቅ ሸፍነው ቀብሩን ፈጽመዋል። የቀብሩ ሥነ-ሥርዓት በሚከናወንበት ወቅት ግን ግለሰቡ ወደ ዩናን ግዛት በማምለጥ ላይ ነበር።
የፖሊስ አባላት ድራማውን በቀላሉ ሊደርሱበት የቻሉት፦የሬሳ ሣጥኑ ግለሰቡ «ከመሞቱ» በፊት በመገዛቱ፣ አደጋው ደረሰበት በተባለበት ወቅት የሕክምና እርዳታ (አምቡላንስ) ወይም ፖሊስ ባለመጠራቱ፣ የሞት ምስክር ወረቀት ወይም ሕጋዊ የቀብር/የቃጠሎ መዝገብ ባለመኖሩ፣ እና የክትትል ካሜራዎች እንዲሁም የባንክ እንቅስቃሴዎች ግለሰቡ በሕይወት መኖሩን በማረጋገጣቸው ነው።
በተደረገው ክትትልም ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር ውሎ የ5 ወራት የእስራት ቅጣት እና የ20 ሺህ ዩዋን (ወደ 3 ሺህ የአሜሪካ ዶላር) የገንዘብ መቀጮ ተጥሎበታል።
በተጨማሪም ወንጀለኛን በመሸሸግ እና በመተባበር ወንጀል በእናቱ እና በአያቱ ላይ የወንጀል ምርመራ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ሀና ሰይፉ
ነሐሴ 05/2018 ዓ.ም
ከሕግ ተጠያቂነት ለማምለጥ የሐሰት ሞት እና ቀብር ያዘጋጀው ቻይናዊ በእስራት እና በገንዘብ ተቀጣ
