ትራምፕ ከደቡብ ኮሪያ ጋር የሚደረገው የጋራ ወታደራዊ ልምምድ እንደሚቀንስ አስታወቁ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር ባላቸው ጥሩ ግንኙነት ምክንያት ከደቡብ ኮሪያ ጋር የሚደረገውን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ “በከፍተኛ መጠን እንደሚቀንሱ” ገለጹ።
 
ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት፤ ደቡብ ኮሪያ ኢራንን ከኒውክሌር መሳሪያ ነጻ የማድረግ ጥረት ውስጥ ለመሳተፍ ፈቃደኛ አለመሆኗን ጠቁመዋል።
 
“እነዚህ ወታደራዊ ልምምዶች እጅግ ውድ ናቸው፤ አብዛኛውን ወጪ የምትሸፍነው ደግሞ እንደተለመደው አሜሪካ ናት። በተጨማሪም ያልተገባና አላስፈላጊ ውጥረት የሚፈጥር መልእክት ያስተላልፋሉ” ብለዋል ትራምፕ።
 
ደቡብ ኮሪያ ግን ከአሜሪካ ጋር የሚደረገው የጋራ ወታደራዊ ልምምድ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንደሚቀጥል አስታውቃለች።
 
ቢቢሲ እንደዘገበው ሰሜን ኮሪያ በጉዳዩ ላይ እስካሁን የሰጠችው አስተያየት የለም። ነገር ግን አገሪቱ በተያዘው ወር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጣለውን እገዳ በመጣስ የባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራ አድርጋለች።
 
ትራምፕ እንዳሉት ለዛሬ የተቀጠረውን ዓመታዊ ወታደራዊ ልምምድ ሙሉ በሙሉ ለመሰረዝ ጊዜው ቢረፍድም፣ ወደፊት ግን እንደሚቀነስ ገልጸዋል። አክለውም “በቅርቡ የደቡብ ኮሪያውን ፕሬዝዳንት ኢራንን ከኒውክሌር ነጻ ለማድረግ እንዲተባበረን ጠይቄው እምቢ ብሎኛል” ሲሉ ጽፈዋል።
 
ትራምፕ ይህን መልእክት ከማሰራጨታቸው ከ24 ሰዓታት በፊት፣ እ.ኤ.አ. በ2019 ከኪም ጆንግ ኡን ጋር የተነሱትን ፎቶግራፍ አጋርተው ነበር።
 
ነሐሴ 11/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *