ማህበሩ “መረጃን ለፖሊሲ ግብአት መጠቀም” በሚል መሪ ቃል ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ የተገኙት ሚኒስትሩ፤ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ሪፎርም ስኬት ጥራት ያለውና ወቅታዊ መረጃ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ዶክተር ካሳሁን አክለውም ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ አጠቃላይ የንግድ ፖሊሲ ማዘጋጀቷን ጠቁመው፤ ከዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) አባልነት ድርድር ጋር ተያይዞም ከ11 ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ የገበያ እድል ስምምነት መደረጉንና ድርድሩ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱን አብራርተዋል።
በሌላ በኩል፣ በበጀት ዓመቱ ከወጪ ንግድ በታሪክ ከፍተኛ የሆነ 11.2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ ይህንን ገቢ ወደ 13.4 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ መሰረት፡ ለ35 ዓመታት የዘለቀውና ከ6 ሺህ 500 በላይ አባላትን ያቀፈው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር፣ በሀገሪቱ የፖሊሲ ቀረጻ ሂደት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ በመድረኩ ላይ ተመላክቷል።
ነሐሴ 11/2018 ዓ.ም
