የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሂደቱን ገለልተኝነት፣ አካታችነትና ተሳትፎ በተመለከተ መግለጫ ሰጠ

 በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ የትኛውንም አካል የፖለቲካ አጀንዳ ለማስፈጸም የሚውል ሳይሆን፣ የሀገሪቱን ጥልቅና ውስብስብ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተከፈተ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን ዛሬ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
 
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በቅርቡ ባወጣው መግለጫ፤ በሂደቱ ላይ የምክክሩን ተዓማኒነት፣ አካታችነት እና ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚከተቱ ተደጋጋሚ ጥፋቶች ተፈጽመዋል ሲል ጠንካራ ቅሬታ አቅርቦ ነበር።
 
ፓርቲው በተለይም የታዩት ግድፈቶች ከተራ የአሠራር ስህተት ያለፉ ናቸው በማለት፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ ውክልና እንደ ዋና ባለቤት ሳይቆጠር መታለፉንና የነዋሪዎች መብት መጣሱን ጠቅሷል። አብን አክሎም እነዚህ ጥሰቶች ካልታረሙ ለምክክሩ ውጤት እውቅና እንደማይሰጥና እንደማይተባበር ማሳወቁ ይታወሳል።
 
ኮሚሽኑ ይህንን የአብን መግለጫ አስመልክቶ በሰጠው ምላሽ፤ አስፈላጊውን ማጣራት ማድረጉንና የተሰጠውን ድምዳሜ እንደማይጋራው አስታውቋል።
 
በምክክር ጉባዔው ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከተቋማት፣ ከቀድሞ ታጣቂዎችና ከዳያስፖራው ጭምር ተወካዮች እየተሳተፉ መሆኑን የጠቀሰው ኮሚሽኑ፤ አብንም ቢሆን እስካሁን በሂደቱ ንቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ ከነበሩ ፓርቲዎች አንዱ መሆኑን አብራርቷል።
 
አክሎም ለሚቀርቡ አቤቱታዎችና ቅሬታዎች በቅሬታ አፈታት ሥርዓቱ መሠረት ምላሽ እየተሰጠ እንደሚገኝና ሂደቱን ለማሻሻል የሚረዱ ገንቢ አስተያየቶችን ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
 
በመጨረሻም ሀገራዊ ምክክሩ የሁሉንም ወገን አሸናፊነት የሚያረጋግጥ በመሆኑ፤ አብንን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላትና መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች በቀሪው የምክክር ሂደት በንቃት እንዲሳተፉ ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅርቧል።
 
ነሐሴ 11/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *