ጥቃቱ የአሜሪካና የቱርክን ውግዘት አስከትሏል፡፡
የሶሪያ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፤ እስራኤል በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ በሚገኝ ወታደራዊ የአየር ማረፊያ ላይ ስምንት የአየር ጥቃቶችን የፈጸመች ሲሆን፤ በጥቃቱም የአውሮፕላን ማረፊያ መንገዱና የቁሳቁስ ማከማቻዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የሶሪያ መንግሥት ቴሌቪዥን የወታደራዊ ምንጭን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ፤ ጥቃቱ ማክሰኞ ማለዳ ላይ በኢድሊብ ግዛት የሚገኘውን የአቡ አል-ዱሁር ወታደራዊ አየር ማረፊያን ኢላማ ያደረገ ነው።
እንደ ሶሪያ ባለሥልጣናት እና በአየር ማረፊያው አቅራቢያ እንደሚኖር ነዋሪ ገለጻ፤ጥቃቱ በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ ቢሆንም በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት የለም።
ሆኖም አንድ ከፍተኛ የእስራኤል ባለሥልጣን ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት፤እስራኤል ከጥቃቱ በፊት ለዋሽንግተን ማሳወቋንና ‹‹በጣም ጥንቁቅ›› የተባሉ የመረጃ ግኝቶችን ማጋራቷን ገልጸዋል።
ይህ ጥቃት ከመጋቢት ወር ወዲህ እስራኤል በሶሪያ መንግሥት ይዞታዎች ላይ የፈጸመችው የመጀመሪያው ጥቃት ሲሆን፣ እ.ኤ.አ በ2024 የፕሬዝዳንት በሽር አል-አሳድ መንግስት ከወደቀ በኋላ በአቡ አል-ዱሁር የጦር ሰፈር ላይ የተሰነዘረ የመጀመሪያው ጥቃት መሆኑ ተገልጿል።
የሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥቃቱን አጥብቆ የኮነነ ሲሆን፤ ድርጊቱን ‹‹ምክንያት አልባ ወረራና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት የጣሰ›› ሲል ገልጾታል።
ደማስቆ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እስራኤል በሶሪያ ግዛት ላይ በየጊዜው በምታደርሰው የሉዓላዊነት ጥሰት ላይ ጠንካራ አቋም እንዲይዝ ጥሪ አቅርባለች።
በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደርና የሶሪያና ኢራቅ ልዩ መልዕክተኛ ቶም ባራክ የተረጋገጠውን የእስራኤል ጥቃት ለቀጣናው መረጋጋት የማይበጅ ‹‹አላስፈላጊ የውጥረት ማባባሻ›› ሲሉ ገልጸውታል።
ቱርክም በበኩሏ ጥቃቱን ያወገዘች ሲሆን፤ ድርጊቱ ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ መሆኑን ገልጻ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በእስራኤል ድርጊት ላይ ጠንካራ አቋም እንዲይዝ አሳስባለች።
በተመሳሳይ ዮርዳኖስም እስራኤልን ‹‹ምክንያት አልባ ወረራ›› የፈጸመችና የሶሪያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የጣሰች ስትል ከሳለች፡፡
የእስራኤል ጦር ስለ ጉዳዩ እስካሁን በይፋ የሰጠው አስተያየት የለም።
እስከዳር ግርማ
ነሐሴ 13/2018 ዓ.ም
