ሕገ መንግሥቱን የሚቃረኑ እና ከነባር ሕጎች ጋር የማይጣጣሙ ረቂቅ ሕጎች ተቀባይነት እንደማይኖራቸው ተገለጸ

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ማንኛውም የሚዘጋጅ ረቂቅ ሕግ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን የማይሸራርፍ መሆኑን የማረጋገጥ ሥራ ቀዳሚ ተግባር መሆኑ ተመለከተ።

የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት የሕግ ማሻሻያና ቁጥጥር ተጠባባቂ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሰፋ ሻረው እንደገለጹት፤ ሕገ መንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ እንደመሆኑ፣ ማንኛውም አዲስ የሚወጣ ሕግ የሕገ መንግሥቱን መሠረታዊ መርሆዎች ተከትሎ መውጣት ይኖርበታል።

አቶ አሰፋ አክለውም፣ በረቂቅ ሕግ ዝግጅት ወቅት በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ መብቶችን የሚጋፋ ወይም ከበላይ ሕጉ ጋር የሚጣረስ ድንጋጌ ከተገኘ፣ ያ ድንጋጌ ተቀባይነት ስለማይኖረው ወዲያውኑ እንደሚሰረዝ አስገንዝበዋል።

አክለውም አዳዲስ ሕጎች ሲወጡ ከነባር ሕጎች ጋር ያላቸውን መጣጣም መፈተሽ ሌላኛው ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል።

ይህም የሚደረገው፣ በነባር እና በአዲስ ሕጎች መካከል የሚፈጠርን የድንጋጌ ግጭት ለማስቀረትና በሕግ አፈጻጸም ሂደት ላይ ሊከሰት የሚችለውን ብዥታ ለመከላከል እንደሆነ ተገልጿል።

ፖሊሲን ለማስፈፀም የሚወጡ ሕጎች በሙሉ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ መርሆዎች ያከበሩ እንዲሆኑ በጥልቀት እንደሚመረመሩም ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል።

ይህም የሕጎችን ተናባቢነት ለመጠበቅና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑ ተመልክቷል።

ልዑል ወልዴ

ነሐሴ 14/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *