በዩክሬን መዲና ኪየቭ ላይ በተሰነዘረ አዲስ የሩሲያ የአየር ጥቃት ቢያንስ 13 ሰዎች ሲገደሉ፤ 40 ያህሉ ደግሞ መቁሰላቸውን የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አስታወቁ።

የዩክሬን አስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት ባወጣው መግለጫ ጥቃቱ የደረሰው ሀገሪቱ ከፍተኛ  የአየር መከላከያ ሚሳይሎች እጥረት ባጋጠማት ወቅት ነው በዚህ እለት በተፈፀመው ጥቃት በመላው  ከተማዋ የሚገኙ የመኖሪያ ሕንጻዎች እና መጋዘኖች የተመቱ ሲሆን  አንድ የሕፃናት ሕክምና ተቁዋም እና ትምህርት ቤትም ጉዳት አስተናግደዋል።

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ የዜጎች ሕይወት ሊያልፍ የቻለው ኪየቭ ከምዕራባውያን ወዳጆቿ የምታገኛቸው የአየር መከላከያ ሚሳይሎች በማለቃቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

የዩክሬን ፓርላማ አባል ኦሌክሲ ጎንቻሬንኮ ለቢቢሲ በሰጡት አስተያየት  ሀገራቸው ከባሊስቲክ ሚሳይል ጥቃቶች “ፍጹም ጥበቃ የላትም” ፤ ሚሳኤሎች ስለሌሉን  “ምንም ማድረግ አንችልም” ብለዋል።

ምክር ቤት አባሉ አክለውም “ሩሲያ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም በተቻለ መጠን ብዙ መሰረተ ልማቶችን ለማውደም እየሞከረች ነው ብለዋል።

ሚሳይሎች ባለመኖራቸው  እና በየቀኑ ሰዎቻችን እየሞቱ በመሆናቸው ሁኔታው ለኛ በጣም አሰቃቂ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በቴሌግራም ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት “ዩክሬን በቂ የባሊስቲክ መከላከያ ሚሳይሎች እስከሌሏት ድረስ ሩሲያ ስለ ሰላም በቁም ነገር አታስብም” ብለዋል።

 አክለውም “ለፓትሪዮት ሥርዓት የሚያገለግሉ ተኳሽ ሚሳይሎች እስካሁን አልተተኩም፤ እነሱ ደግሞ በየቀኑ ያስፈልጉናል። እያንዳንዷ ተጨማሪ ሚሳይል የሕዝባችንን ሕይወት ታድናለች” ሲሉ አስገንዝበዋል።

የዩክሬን አየር ኃይል ባወጣው የቅርብ ጊዜ መረጃ  በሌሊቱ ጥቃት ከተተኮሱት የሩሲያ ባሊስቲክ ሚሳይሎች መካከል አንዱንም ማክሸፍ አለመቻሉን ጠቁሟል።

በሌላ በኩል የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ፣ ወታደራዊ ተቋማትንና መጋዘኖችን  ለማጥቃት በአየር፣ በየብስ እና በባሕር ላይ የተመሰረቱ የጦር መሣሪያዎችን ጥቅም ላይ ማዋሉን አረጋግጧል።

ዩክሬን የሩሲያን ባሊስቲክ ሚሳይሎች ለመመከት በአሜሪካ በሚቀርቡላት የፓትሪዮት መከላከያ ሚሳይሎች ላይ ጥገኛ የነበረች ቢሆንም  አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ምክንያት አብዛኛውን ክምችቷን በመጠቀሟ ለዩክሬን የምታቀርበውን መጠን ለመቀነስ ተገዳለች።

ሀና ሰይፉ

ነሐሴ 14/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *