ኩባንያው በኢትዮጵያ ባለፉት 15 ዓመታት ከ1 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ኢንቨስት አድርጓል።
ሃይኒከን ኢትዮጵያ በሀገሪቱ ያደረገውን የ15 ዓመት የኢንቨስትመንት እና አጋርነት ጉዞውን “15 ዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ ማደግ” በሚል መሪ ቃል በቂሊንጦ ፋብሪካው ትላንት አክብሯል፡፡
በክብረ በዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት የሃይኒከን ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ባርት ዲ ኬኒንክ እንደገለጹት፤ ኩባንያው ባለፉት 15 ዓመታት ከ1 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ኢንቨስት አድርጓል። እንዲሁም ሃይኒከን ኢትዮጵያ ስምንት ተከታታይ ዓመታት የሀገሪቱ ከፍተኛ የግል ግብር ከፋይ በመሆን ከ103 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማድረጉ ተገልጿል።
ኩባንያው በግብርናው ዘርፍም ከ120 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን፣ ከ2023 ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ሀገር በቀል ገብስ በመጠቀም የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት ተችሏል ብለዋል ዋና ስራ አስፈጻሚው ።
ኩባንያው በቀጥታ እና በእሴት ሰንሰለቱ ከ137 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፤ በህብረተሰብ ልማት ሥራዎቹም ከ82 ሺህ በላይ ሰዎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል።
በተጨማሪም የቂሊንጦ ፋብሪካውን ሙሉ በሙሉ ታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ በማድረግ በካርቦን ነፃ አሰራር ቀዳሚ ለመሆን ማቀዱን ይፋ አድርጓል። በዕለቱ ለ15 ዓመታት የጉዞ አጋር ለነበሩ ተቋማትም እውቅና ተሰጥቷል።
ነሐሴ 27/2018 ዓ.ም
ሃይኒከን ኢትዮጵያ “15 ዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ ማደግ” በሚል መሪ ቃል አከበረ
