የአሜሪካ ልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን በኢትዮጲያ አዳዲስ የሥራ እድሎችን ለመፍጠር እንደሚሰራ የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታወቁ

የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀዋል
 
የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ጋርሺያ የንግድ ዲፕሎማሲን፣ የጸጥታ ትብብርን እና ቀጣናዊ ሰላምን ለማጠናከር በኢትዮጵያ ያደረጉትን የአምስት ቀናት ጉብኝት ማጠናቀቃቸውን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ አስታወቀ።
 
ረዳት ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ጋር ተገናኝተው በአፍሪካ ቀንድ ሰላም ማስፈን እና የጠላትነት ማቆም ስምምነትን (COHA) ሙሉ በሙሉ መተግበር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ተወያይተዋል።
 
ኤምባሲው ለጣቢያችን በላከው መግለጫ በተጨማሪም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ጋር በቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ግንባታ ቦታ በመገኘት፣ የአየር መንገዱን የአውሮፕላን ስብስብ በዘመናዊ የአሜሪካ ቴክኖሎጂ ለማደስ በሚደረገው ጥረት ላይ መክረዋል።
 
በቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ረዳት ሚኒስትር ጋርሺያ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ የሱፍ እና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ መልእክተኛ ፔካ ሀቪስቶ ጋር በመገናኘት፣ በሱዳን የተኩስ ማቆም ስምምነት ለማውረድና የሰብአዊ እርዳታን ተደራሽ ለማድረግ በጋራ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መነጋገራቸውን ጣቢያችን ከኤምባሲው መግለጫ መረዳት ችሏል።
 
በኦሮሚያ ክልል ባደረጉት ጉብኝት ከክልሉ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ እና ከሻሸመኔ ከንቲባ አዳነ ተክለ ጊዮርጊስ ጋር ተገናኝተው የአሜሪካ የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና የጆን ዲር (John Deere) ማሽነሪዎችን አጠቃቀም ተመልክተዋል።
 
በመጨረሻም ረዳት ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ እድገትና ደህንነት በጥብቅ የተሳሰሩ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ከአሜሪካ የንግድ ምክር ቤት ጋር ተወያይተዋል።
 
በዚህም የአሜሪካ ልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (DFC) ለቢሾፍቱ አየር መንገድ ግንባታ እና ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚሰጠውን የብድር ድጋፍ በማስፋፋት አዳዲስ የሥራ እድሎችን ለመፍጠር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
 
ጳጉሜ 3/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *