2ኛው ታላቁ የኢሬቻ ሩጫ ውድድር መስከረም 21 ቀን በቢሾፍቱ ከተማ ሊካሄድ ነው

ሁለተኛው የታላቁ ኢሬቻ ሩጫ ውድድር በቢሾፍቱ ከተማ በደመቀ ሁኔታ እንደሚካሄድ የኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

ውድድሩ “ኢሬቻ ወሊገልቴ ብያለሳፍ” ( ኢሬቻ ለሃገራዊ መግባባት ) በሚል መሪ ቃል በመጪው መስከረም 21 ቀን እንደሚከናወን የተገለጸ ሲሆን፤ ከበዓሉ አከባበር ጋር ተያይዞ የተዘጋጀው ይኸው መርሐ ግብር በላቀ ሁኔታ መጠናቀቁና በስፖርታዊ ጨዋነት እንደሚካሄድ ተመላክቷል።

የኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ብያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ የማንነቱ፣ የነፃነቱ፣ የአንድነቱና የሰላሙ ትልቅ መገለጫ ነው።

አክለውም ስፖርት ፍቅርን፣ አንድነትንና ወንድማማችነትን ይበልጥ የሚያጠናክር በመሆኑ ከኢሬቻ እሴቶች ጋር ተጣጥሞ እንደሚሄድና የበዓሉን ድምቀት እንደሚያጎላው አስገንዝበዋል።

በዘንድሮው የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ላይ ከ1 ሺህ 400 በላይ ፕሮፌሽናል አትሌቶች እንዲሁም ከ50 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ተገልጿል።

ለአሸናፊዎችም ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት የተዘጋጀ ሲሆን፤በሁለቱም ጾታ 1ኛ ለሚወጡ አትሌቶች 1 ሚሊዮን ብር፣2ኛ ደረጃን ለሚያገኙ 750 ሺህ ብር፣3ኛ ለሚሆኑት ደግሞ 500 ሺህ ብር እንደሚበረከት ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ እስከ 6ኛ ደረጃ ድረስ ለሚያጠናቅቁ አትሌቶችና በሕዝብ ሩጫው ለሚሳተፉ አካላት የገንዘብና የሜዳሊያ ሽልማት እንደሚሰጥ ተጠቁሟል።

በመግለጫው ወቅት አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎችና ጥሪ የተደረገላቸው አምባሳደሮች የተገኙ ሲሆን፤ በውድድሩ ላይ ታዋቂዋ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባን ጨምሮ በርካታ ተፅዕኖ ፈጣሪ አትሌቶች በአምባሳደርነት እንደሚሳተፉበት ኃላፊዋ ወይዘሮ ሮዛ ብያ አስታውቀዋል።

ልዑል ወልዴ

መስረከረም 8/2019 ዓ›ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *